የዓለም ዋንጫ አዲስ አበባ ገባ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) በ2022 በኳተር የሚደረገው የዓለም የእግር ኳስ ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ በተለያዩ አገራት ለእይታ የሚቀርበው የዓለም ዋንጫ ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
ብራዚላዊው የባርሴሎና የቀድሞ ተጫዋች ጁሊያኖ ቤሌቲ ዋንጫውን ይዞ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ዋንጫው ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ፣ የባህልና ስፖርት የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች በመገኘት አቀባበል አድርገዋል።
በኳታር በሚካሄደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ አስቀድሞ በተለያዩ ሀገራት የዓለም ዋንጫው ለእይታ ይቀርባል።
የዓለም ዋንጫው በአፍሪካ ዘጠኝ አገራት ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን የመጀመሪያ መዳረሻው ኢትዮጵያ ሆኗል።
ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ ኤርፖርት ወደ ቤተ -መንግሥት በመጓዝ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የዋንጫ ርክክብ ፕሮግራም ይደረጋል።
ዋንጫው ነገ በመስቀል አደባባይ እና በተመረጡ ቦታዎች ለእግር ኳስ አፍቃሪዎች ለእይታ እንደሚቀርብ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዓለም ዋንጫው በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የዘንድሮው ለሦስተኛ ጊዜ ነው።
32 አገራት የሚሳተፉበት የኳታሩ የ2022 የፊፋ ዓለም ዋንጫ በኅዳር ወር 2015 ዓም ይካሄዳል።