የዓድዋ ድል በዓልን ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 22/2014 (ዋልታ) የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ በድምቀት ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
በነገው ዕለት 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ ለኢትጵያዊያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ!” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበር ሲሆን የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓል ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ በድምቀት ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በዚህም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ክልል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና አባት አርበኞች በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙና የፌዴራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግስተ የሥራ ኃላፊዎች፣ አባት አርበኞች እና መላው የከተማችን ነዋሪ በሚገኙበት በእግር ጉዞና በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች ከሚኒሊክ አደባባይ እስከ ዓድዋ ድልድይ እንሚከናወኑ ጠቁሟል፡፡
የዓድዋ ድል የአንድነት ውጤት መሆኑን በማስታወስ እንዲሁም ከኛም አልፎ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አርማ ስለሆነ ጥቃቅን ልዩነቶችን ለማጉላት ከመሥራት ተቆጥበን ያለምንም ልዩነት እንደ አባቶቻችን በአንድነት ስሜት በጋራ ማክበር ይገባናልም ብሏል በመግለጫው።
በዚሁ መሰረት በማለዳ በሚኒሊክ አደባባይ በሚደረገው የመክፈቻ ሥነስርዓት ተጀምሮ ወደ ሌላኛው ታሪካዊ ቦታ ወደ ዓድዋ ድልድይ በእግር ጉዞ እንደሚቀጥልና በመጨረሻም በዓድዋ ድልድይ በሚደረጉ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል፡፡