የዓድዋ ድል እና የውጭ ጋዜጦች

የዓድዋ ድል እና የውጭ ጋዜጦች
 
(በአመለወርቅ መኳንንት)
 
የካቲት 22/2014 (ዋልታ) የዓድዋ ድል በሺሕ ዘመናት ግዙፍ ታሪኳ፣ ገናና ሥልጣኔ ዋና አኩሪ ባህሏ ለምትታወቀው፣ በነጻነቷና በሉዓላዊነቷ ጸንታ ለኖረችው ኢትዮጵያ ዳግመኛ በዓለም መድረክ ለአፍሪካውያን፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት አለኝታ፣ የወኔ ስንቅና ሰው የመሆን ከፈጣሪ ዘንድ የተቸረ መለኮታዊ ፍቅርንና ክብርን ከፍ ያደረገ ድል ነው፡፡
 
በርግጥም ኔልሰን ማንዴላ በንግግራቸው ለመጥቀስ እንደሞከሩት ዓድዋ- ለኢትዮጵያዊነት ዝርግፍ ጌጥ የተደነቀ ውበት፣ ሰው የመሆን ክብርንና የመንፈስ ልዕልናን ያጎናጸፈ፣ የዘረኝነት እኩይ እሳቤና የቅኝ ግዛት ቀምበርን የሰበረ አንፀባራቂ ድል ነው!
 
በዚህም ከአድዋ በፊት በነበሩ ዓመታት በርካታ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ጋዜጦች መላው ጥቁር አፍሪካ በአውሮፓ ሙሉ ቁጥጥር ስር ለመሆን መቃረቡን በእርግጠኝነት ይፅፉ ነበር የአሜሪካው አትላንታ ኮንስቲትዩሽን ጋዜጣ ‹‹መላዉ አፍሪካ በአውሮፓ መንግስት ቅርምት የምትጠናቀቅበት ቀን ቀርቧል›› የሚል ሐሣብ የያዘ ጽሑፍ አስፍሮ ነበር፡፡
 
“አውሮፓውያኑ በአሜሪካ ያሳኩትን የዘር የበላይነት በአፍሪካ ለመድገም ተዘጋጅተዋል፡፡ በአሜሪካ ቀይ ህንዶችን በማስወገድ ለራሳቸው ዝርያ መኖሪያ መፍጠር የቻሉበትን ብቃት በአፍሪካም እውን ለማድረግ የጥቁር አፍሪካ ዝርያዎችን በቅርቡ ማጥፋት ይጀምራሉ፡፡” እያሉ በአውሮፓ የዘር እና የፖለቲካ የበላይነት ዲስኩሮቻቸው ዝተው ነበር፤ ነገር ግን እንዳሰቡት ሳይሆን ቅዠት ሆኖ ቀርቷል፡፡
የአትላንታው ኮንስቲትዩሽን ጋዜጣ በመጋቢት 1/1896 እትሙ ወደ አፍሪካ የመመለስ አላማ ለነበራቸው ጥቁር አሜሪካውያን የሚሆን መልዕክት ይዞ ነበር የወጣው፡፡ በእትሙ ያሰፈረው ሀሳብ ከጆርጂያ ወደ አፍሪካ የመመለስ ፍላጎት የነበራቸው ጥቁር አሜሪካውያንን አስጠንቅቋል፡፡ አፍሪካ ሙሉ በሙሉ በነጭ አውሮፓውያን ቁጥጥር ስር በመዋሏ የጥቁር አሜሪካውያን መልስ ጉዞ ውጤት አልባ መሆኑን አስነብቧል፡፡
የአድዋ ድል ዜና በአለም በተሰማ ማግስት ግን ይኸው የአትላንታው ኮንስቲትዩሽን ጋዜጣ ሚዛናዊ የሆነ ዜና አውጥቷል፡፡ ጋዜጣው በመጋቢት 4 እትሙ ‹‹የጣልያን ክፉ እጣ›› በሚል ርዕስ ያወጣው ጽሑፍ 3ሺህ የጣልያን ወታደሮች በአቢሲንያ ህዝቦች መገደላቸውን አስነብቧል፡፡
 
ጽሑፉ ጄነራል ኦሬስቴ ባራቴሪ በከፍተኛ ውርደት ራሱን ማጥፋቱን የገለፀ ሲሆን ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ የምትገኝ ሀገር መሆኗን አሳስቶ ጠቅሷል፡፡ በተከታታይ የወጡ የአትላንታው ኮንስቲትዩሽን ጽሑፎች በኢትዮጵያውያን የቆዳ ቀለም ላይ ያተኩሩ ነበር፡፡
 
የኢትዮጵያ ንጉስ አፄ ሚኒሊክ ከኒኮላስ ሁለተኛ ተመሳሳይ መልክ አላቸው ሲልም በጽሑፉ የንጉሱን ውበት በማድንቅ አስፍሯል፡፡
ኒዮርክ ወርልድ እና ቺካጎ ትሪቢውን ጋዜጦችም ተመሳሳይ ጽሑፎችን አውጥተው ነበር፡፡ አፄ ሚኒሊክ ነጭ ቀለም እንዳላቸው የሚያሳዩ ፎቶዎችን በማስደገፍ የካውካስያን ዝርያ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጣልያንን የማሸነፋቸውን ዜና ለአለም አስታውቀዋል፡፡
 
“የአቢሲንያ ህዝቦች በአብዛኛው የተስተካከለ የፊት ቅርፅ ያላቸው ቆንጆ ህዝቦች ናቸው” ሲልም ከጀግንነት ባለፈ ስላላቸው ውበትም አስነብቧል፡፡ በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ገናና የነበረው ቫኒቲ ፌየር የተሰኘው መጽሄት በ1897 ባሰፈረው የፊት ገጹ ላይ የአፄ ሚኒሊክን ምስል ይዙ በመውጣት የንጉሱን አኩሪ ጀግንነት ለመላው አለም አስተዋውቋል፡፡
 
መጽሔቱ ከቻርሊስ ዳርዊን፣ ከሩስያው አሌክሳንደር እና ናፖሊዮን ሳልሳዊ እኩል የአፄ ሚኒሊክን ፎቶ ግራፍ ተከትሎ የአፄ ሚኒሊክ እና የእቴጌ ጣይቱ በአለም ከታዋቂ እና ዝነኛ ግለሰቦች ተርታ አሰልፎ አስነብቧል፡፡ የአፄ ምንሊክን እና የእቴጌ ጣይቱ ዝና እና ጀግንነት መናኘቱን ተከትሎ የተለያዩ አዳዲስ ክስተቶች በዓለም ታይተዋል፡፡
በዚህም በርካታ አውሮፓውያን አዳዲስ የተወለዱ ልጆቻቸውን ‹‹ምኒሊክ›› የሚል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሚኒሊክ ሆቴል ጅቡቲ፣ ሚኒሊክ ጎዳና እንግሊዝ-ለንደን፣ ሚኒሊክ ጋዜጣ ብራዚል፣ ሚኒሊክ ሽቶ ደቡብ አፍሪካ፣ ሚኒሊክ ቢራ ቤልጅየም፣ ሚኒሊክ ቸኮሌት ፈረንሳይ የተሰኙ ድርጅቶች ከብዙ በጥቂቱ ተሰይመዋል፡፡
 
ከዓደዋ ድል በኋላ መላው ዓለም የኢትዮጵያን የንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ለማግኘት መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ የፈረንሳይ ጋዜጦች ከአደዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ልዕለ ኃያል እየሆነች መምጣቷን ገልፀዋል፡፡
የዚህ ድል ዜማም በዓለም ዙሪያ ሁሉ ከፍ ብሎ ተሰማ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ጋዜጦችም ድሉን አስመልክተው በፊት ገጾቻቸው ዘገቡ፡፡
 
ቪቫ ኢትዮጵያ! ቪቫ ሚኒልክ! ቪቫ ጣይቱ! የሚሉ የድል ብስራቶችና ዜናዎች በመላው ዓለም ናኙ፡፡ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በዓድዋው የድል ስሜትና፣ በኢትዮጵያዊነት የነጻነት ተጋድሎ ስሜት የተረገዙ ንቅናቄዎችም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡
 
ጥቁር መሆን እንደ ወንጀልና ክህደት በተቆጠረበት አስከፊ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ከእንሰሳ ያነሰ ክብር እንኳን በተነፈገበት፣ አፍሪካውያን የጨለማና እንደ መርግ በከበደ የመከራ ዘመን የሰው ልጅ ሕሊና ሊሸከመው የማይችል ውርደትና መከራን አሳልፈዋል፡፡
 
ለዘመናት በእንዲህ ዓይነት መከራ ጀርባዋ ለጎበጠው አፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ እናት አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ በናፍቆትና በሰቀቀን የሚያስቧት፣ በዘላለም ቃል ኪዳን በልባቸው ጽላት የተጻፈች፣ የታተመች ከሩቅ አሻግረው የሚያይዋት አፍሪካዊት የነጻነት ቀንዲል፣ የነጻነታቸውና የሉዓላዊነታቸው ተስፋቸው፣ ከነዓናቸው ነበረች – ኢትዮጵያ!
 
ኢትዮጵያን በብዙዎች አፍሪካውያንና በመላው የጥቁር ሕዝብ ዘንድ የነጻነታቸው ተስፋና ብርሃን ተምሳሌት ሆና ከፍ ብላ እንደትታይ ያደረጓት የበርካታ ጀግኖች እናት ናት፡፡ በሺሕ ዘመናት የሚለካው ታሪኳ፣ ጥንታዊና ገናና የሆነ ሥልጣኔዋ፣ ነጻነታቸውን አፍቃሪ ለሆኑ የዓለም ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነው የልጆቿ የአይበገሬነት ጽኑ የነጻነት መንፈስ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሣው አንጸባራቂው የዓድዋው ድል በግንባር ቀደምትነትና በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡
 
ዓድዋ በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው ሲማቅቁ ለነበሩ ለአፍሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተስፋ ጮራን የፈነጠቀ፣ ለነጻነት ታጋዮች ትልቅ ወኔንና መነቃቃት የፈጠረ ታላቅ ድል ነው!
 
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!