የዘንድሮው ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14 መሆኑን ቦርዱ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – የ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሰኔ 14 መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ምርጫው ሙሉ ለሙሉ የመራጮች ምዝገባ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የመራጮች ምዝገባ ያልተከናወነባቸው፣ አቤቱታ የቀረበባቸውና ቦርዱ የምዝገባ ሂደቱ ወጥነት ይጎድለዋል ባላቸው አካባቢዎች ውሳኔ የሚሹ በመሆናቸው በተጠቀሰው ቀን እንደማይካሄድ ገልጸዋል።

ከነዚህ መካከል በሶማሌ ክልል ከመራጮች ምዝገባ ሂደት ጋር በተያያዘ አቤቱታ በቀረበባቸው 7 የምርጫ ክልሎች፣ ሃረሪ ክልል፣ መተከል ዞንና ሌሎች የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባዎች በተጠቀሰው ቀን የማይካሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የድምጽ መስጫ ቀን የተራዘመው በእለቱ የሚያስፈልጉ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመልና ስልጠና ለመስጠት እንዲሁም ለድምጽ መስጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስን ለመላክ መሆኑን አውስተዋል።