የዘንድሮው የካብ ኦፍ ኤክሰለንስ የቡና ውድድር አሸናፊዎች ይፋ ሆኑ

ግንቦት 16/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ከአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ጋር በመተባበር የ2013 ካብ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር የኢትዮጵያ ምርጥ 30 አሸናፊዎች ይፋ ሆነዋል።
በዘንድሮው የካብ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ከ1ሺህ 848 በላይ የቡና ናሙናዋች ለሰባት አለም አቀፍ ሀገራት ተልከው ለውድድር የቀረቡ ሲሆን አርባ ናሙናዎች አሸናፊ ሆነዋል።
በዘንድሮው የካብ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር አቶ ታምሩ ታደሰ ከሲዳማ ክልል በንሳ ዞን 90 ነጥብ 06 በማግኘት ውድድሩን በአንደኝነት ለማጠናቀቅ ችለዋል።
ኮቪድ-19 ባስከተለው የጉዞ ገደብ እና ተያያዥ ክልከላዎች የዘንድሮው ካብ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር የመጨረሻ ሁለት ዙሮች ከኢትዮጵያ ውጭ መካሄዳቸው አለም አቀፍ ገዥዎች በአካል ተገኝተው ግብይት እንዳያካሂዱ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።
137 አለም አቀፍ የቡና ገዥዎች በሰኔ 18 በአሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ድረ ገፅ ላይ ለ24 ሰዓታት በሚካሄደው ጨረታ ለመሳተፍ መመዝገባቸው ተገልጿል።
ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ በተካሄደው የካብ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር ለዘርፉ በርካታ ጥቅም ያስገኛል ያሉት ደሳለኝ ጀና የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ በበቂ ሁኔታ ባለመታዋወቁ ተመጣጣኝ ገቢ ሊያስገኝ አልቻለም ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በተደረገው ውድድር የውድድሩ አሸናፊ ቡና በቀጥታ ጨረታ በኪሎ 407 የአሜሪካ ዶላር በመሸጥ የኢትዮጵያን የቡና ዋጋ ሪከርድ መስበሩ ይታወሳል።
(በቁምነገር አህመድ)