ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) “በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የተገኘው ድል ባለቤት ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን ሲሉ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት አማካኝነት የሚካሄደው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ “ኅልውናን መጠበቅ፣ ዕድገትን ማዝለቅ” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድሪኩ ላይ የተገኙት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በአሸባሪው አካል መጠነ ሰፊ ረሀብ፣ ጾታዊ ጥቃት እና ሰብዓዊ ርዳታን ለጦርነት መጠቀም አጀንዳ ተቀርጾ ተጨማሪ ትረካ ታክሎበት ለፕሮፖጋንዳ ግብዓት ሆኗል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ “ኅልውናን መጠበቅ፣ ዕድገትን ማዝለቅ” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ባለው የአዲስ ወግ ውይይት እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ፖለቲካዊ ዓላማ የሌላቸው አካላት አዲስ አበባን እንደ ከበቡ ማስመሰላቸውን አስታውሰዋል።
ከውስጥ እና ከውጪ በተቀናጀ መልኩ ሕገወጥ የመሣሪያ፣ የገንዘብና የደንብ ልብስ ዝውውር እንዲሁም የሕግ አስከባሪ አካላት የደንብ ልብስ ዝውውር አድርገዋል ያሉት ሚኒስትሩ ሕዝቡን በስነልቦና እና በፕሮፖጋንዳ ለማሸበር ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀናጀ ዕቅድ የአመራር ቅንጅት በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል፣ የትጥቅ እና የስንቅ ዝግጅት ማድረጉንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርብ ሆነው ለመምራት ወደ ግንባር በመግባታቸው በሁለት ሳምንታት ውስጥ የአሸባሪውን ኃይል ዕቅድ ለማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።
የመንግሥት የመረጃ ፍሰት እና አሰጣጥ ከአንድ ሰው የሚወጣ ያህል ተጠናክሮ እየተከወነ ነው፤ የዚህ ሁሉ ድል ባለቤት በመላው ዓለም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ነን ሲሉ በመድረኩ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው በሁኔታው ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚሠሯቸውን ዘገባዎች ዓይነት እና ድምዳሜ አስቀድመው ይወስኑ እንደነበርና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ሚዛኑ ለሌላኛው አካል እንዲያጋድል ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ከውጪና ከውስጥ ያለውን ግፊት የምትቋቋምበት አቅም ፈጥሯል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ይህ ጫና ከኢትዮጵያ ባለፈ አፍሪካ ባለችበት እንድትረግጥ የታሰበ መሆኑን ተገንዝበው ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን አሳይተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የውጪ ግንኙነት የውስጥ ሁኔታ ነጸብራቅ ስለሆነ የውስጡን የሰላምና የኢኮኖሚ ሁኔታ ስናስተካክል ነው በማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለይም ዳያስፖራው ሀገራት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላቸው አቋም የጠራ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
መረጃውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው ያገኘነው፡፡