ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ክልል የከምባታ ጠምባሮ ዞን እና የም ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የድጋፍ ሰልፍ አካሄዱ፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አሸባሪው የህወሃት ቡድን ትንኮሳን አከሽፎ የህግ የበላይነትን እያስከበረ ያለውን ተግባር በሙሉ ልብ እንደሚደግፉ ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡
የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህፃናት የጦር መሳሪያ በማሸከም ሀገር ለማፈራረስ እየሰራ ያለውን ሰራ አጠብቀው አውግዘዋል፡፡
በቀጣይ ጊዜያት እንደዚህ ዓይነት ድርጊት እንዳይፈፀም መንግስት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የጠየቁት ነዋሪዎቹ፣ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር ሀገርን ለማፍረስ እየሰራ ያለው ተግባር አስፀያፊ ድርጊት በመሆኑ በህግ ሊጠየቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ መንግስት በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ላይ የህግ በላይነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ተግባር ውጤታማ እንዲሆን በሞራል፣ በገንዘብ፣ በሀሳብ፣ በስንቅና በተለያዩ የድጋፍ አግባቦች ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ፈተናዎችን እየመከትን የተስፋ ብርሃናችንን ለማድመቅ እንሰራለን፣ የአሸባሪውን የህወሃት ትንኮሳ እናከሽፋለን፣ ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿ በላይ ኃያል ናት፣ የአድሎ እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ፣ እውነትና ፍትህ ለኢትዮጵያ፣ ብሔራዊ ጥቅማችንንና ሉዓላዊነታችን ይከበር፣ እኔ የጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ደጀን ነኝ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደማቅ አሻራችን ነው፣ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች፣ የጦር መሣሪያ ከትግራይ ህፃናት ትከሻ ይውረድ የሚሉና መሰል መልዕክቶችን በማስተጋባት የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
የየም ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል ለሰልፉ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ላይ የጀመረውን የህግ የበላይነት የማስከበር ተግባር ግቡን እንዲመታ የልዩ ወረዳው ህዝብ እና መንግስት በሙሉ ልብ እየደገፉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ይህ የድጋፍ ሰልፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተደረገ ማግስት በመሆኑ ከሌሎች ጊዜያት ልዩ እንደሚያደርገው የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ የልዩ ወረዳው መንግስትና ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ከመስጠት ጀምሮ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች እንደሀገር የተጀመረው ሁለንተናዊ ብልፅግና ግቡን እንዲመታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ዋና አስተዳዳሪው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን፣ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንደተጠናቀቀ ከየም ልዩ ወረዳ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተመሳሳይ ዜና ከምባታ ጠምባሮ ዞን ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች እና ሚሊሻዎች የሕወሓት ኃይል በሀገሪቱ ላይ የቃጣውን ትንኮሳ በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል።
በሰልፉ የጦር መሣሪያ ከትግራይ ሕፃናት ትከሻ ይውረድ፣ እኛ የመከላከያ ደጀን ነን፣ ፈተናዎችን እየመከትን የተስፋ ብርሃናችንን እናደምቃለን፣ ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿ በላይ ናት የሚሉ እና መሰል መፈክሮችን ማሰማታቸውን ደሬቴድ ዘግቧል።