የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ባለሃብቶችን በማስተባበር ከ4ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች የበዓል ቁሳቁስ ድጋፍ አደርጓል፡፡
ክፍለ ከተማው በግ፣ ዶሮ፣ ዘይት፣ ዱቄት፣ ሽንኩርትና እንቁላልን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ግብዓቶች ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ለዚህም ከ8 ሚሊየን ብር ላይ ወጪ ሆኗል፡፡
የክፍለከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ ይህ ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሃብችና በበጎ ፈቃድ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ነዋሪዎችም በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 149 ለሚሆኑ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች ለእያንዳንዳቸው 1ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ፣ 1 ዶሮና 12 እንቁላል፣ ለ60 ከየወረዳው የተውጣጡ አቅመ ደካሞች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የአንድ በግ የገና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በክፍለ ከተማው የተለያዩ ወረዳዎች የሚኖሩ ጧሪ የሌላቸውና አቅመ ደካሞች ቤት የማደስ ስራ የተሰራ ሲሆን፣ ቤቶቹን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና የክፍለከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ ለነዋሪዎቹ አስረክበዋል፡፡
(በነስረዲን ኑሩ)