የዩኬ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጠል ተጠየቀ

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የልማት ድጋፍ ወደቀደመው መጠኑ እንዲመለስ የእንግሊዝ ፓርላማ ጥምረት ቡድን ግፊት እንዲያደርጉ ተጠየቀ፡፡
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በፓርላማ ተገኝተው ለእንግሊዝ ፓርላማ ጥምረት ቡድን አባላት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት ከአውሮፓ መውጣቱን ተከትሎ በካሄደው የውጪና የመከላከያ ፖሊሲ ክለሳ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ሀገሮች ዋናዋ እንደነበረች ያስታወሱት አምባሳደር ተፈሪ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱም በተገባው ቃል መሰረት እንዲቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
አምባሳደር ተፈሪ አያይዘውም የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ኢትዮጵያ በፖሊሲና በእቅድ የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ቀርጻ ከራሷ በማለፍ ለጎረቤት አገራት እና ለአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ድጋፍ እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ያደጉ አገራት የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር በማደግ ላይ ላሉ አገራት የሚደረግ ድጋፍ በተገባው ቃል መሰረት እንዲፈጸም የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የጀመረውን ግፊት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የልማት ድጋፍና ትብብሩ በትምህርት፣ በጤና፣ በእናቶችና ሕጻናት እንዲሁም በማኅበራዊ ዘርፎች መሆኑን አስታውሰው በርካታ ውጤታማ ተግባሮች መከናወናቸውን አመልክተዋል። ሆኖም ግን የድጋፍ መጠኑ በመቀነሱ በእቅድ የተያዙ የማኅበራዊ አገልግሎቶች አፈጻጸምን እንዳጓተተ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!