የደም ማነስ በሽታና መፍትሄዎቹ



የደም ማነስ በሽታ ሰውነታችን ከሚያስፈልገው ቀይ የደም ሴል ቁጥር በታች ሲሆን የሚፈጠር የጤና ችግር ነው። የደም ማነስ ችግር ያለበት ሰው ሰውነቱ በቂና በኦክሲጅን የበለጸገ ደም አያገኝም። ሰውነታችን በቂ ኦክሲጅን የማያገኝ ከሆነ ደግሞ የድካም ስሜትና የመዛል ሁኔታ ያጋጥመናል።

በዚህ ምክንያትም የትንፋሽ ማጠር፣ መዛል፣ የራስ ምታት እና የተዛባ የልብ ምት (Irregular heart beat) ይኖረናል።

የደም ማነስ በሽታ መለስተኛ ወይም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። መለስተኛ የሚባለው የደም ማነስ በሽታ በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚከሰትና ከአመጋገብ፣ ከምንወስደው የመድኃኒት ዓይነትና ተያያዥ ችግሮች የተነሳ የሚያጋጥም ሲሆን ከፍተኛ የሚባለው ደግሞ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና ቶሎ የማይለቅ የደም ማነስ ዓይነት ነው። አንዳንድ የደም ማነስ በሽታ ከዘር የሚወረስ ስለመሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የደም ማነስ በሽታ ዓይነቶች

ሀ. ለሰውነታችን ከሚያስፈልገው የብረት ማዕድን እጥረት የሚመጣ የደም ማነስ (Iron-deficiency anemia) – በጣም የተለመደውና በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚከሰተው የደም ማነስ ዓይነት ሲሆን ማዕድኑን በበቂ ሁኔታ የማንወስድ ከሆነ ወይም ሰውነታችን ከተመገብነው ምግብ ላይ ማዕድኑን በበቂ ሁኔታ መምጠጥ ሳይችል ሲቀር ያጋጥማል። በእርግዝናና በወሊድ ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ማዕድን ጥቅም ላይ ስለሚውል በእርግዝና ወቅት የደም ማነስ በሽታ እንዲፈጠር ያደርጋል።

ለ. ከቫይታሚን እጥረት የሚመጣ ደም ማነስ ፡- ይህ ዓይነቱ በሽታ ከቫይታሚን ቢ-12 (ፎሊክ አሲድ) እጥረት የሚከሰት ሲሆን በምግባችን ውስጥ በቂ ቫይታሚን ሳይኖር ሲቀር እንዲሁም ከልመት ሥርዓት በበቂ ሁኔታ ወደ ሰውነታችን መቀላቀል ሲያቅት የሚመጣ የደም ማነስ ዓይነት ነው።

ሐ. በመቅኔ ውስጥ በሚፈጠር ችግር የሚመጣ የደም ማነስ (Aplastic Anemia) ፡- ከተላላፊ በሽታዎች፣ ከራዲየሽንና ከመርዛማ ንጥረ ነገር ተጋላጭነት የሚከሰት ሲሆን መቅኔያችን በበቂ ሁኔታ ቀይ የደም ህዋሳቶችን ለማምረት ችግር ይገጥመዋል። በመቅኔያችን ውስጥ የደም ህዋሶችን ለማምረት የሚችሉት ደም አምራች ህዋሶች በኬሚካሎችና በራዲየሽን ምክንያት ጉዳት ስለሚደርስባቸው የተለመደ የማረት ተግባራቸውን ማከናወን አይችሉም።

መ. ሄሞሊቲክ የደም ማነስ ፡- ሰውነታችን ከሚያመርተው ቀይ የደም ህዋሳት ቁጥር ከአገልግሎት ውጭ የሚሆኑት ቁጥር ሲያንስ የሚፈጠር ችግር ነው። የዚህ ችግር መንስኤው በዋናነት በመቅኔ ላይ የሚፈጠር ጉዳት፣ በበሽታ ምክንያት ወይም የሰውነት በሽታ የመከላከል ስርዓት፣ ጤናማ የአካል ክፍሎችን እና ህዋሶችን በስህተት ሲያጠቃ (autoimmune diseases) የሚፈጠር ነው።

ሠ. ሲክል ሴለ አኒሚያ፡- በዘር የሚተላለፍ የደም ማነስ በሽታ ዓይነት ሲሆን በሄሞግሎቢን መዛባት ምክንያት የሚፈጠረው ቀይ የደም ህዋስ በጥቃቅን የደም ስሮቻንን በመዝጋትና ፍሰትን በማስተጓጎል ደም በበቂ ሁኔታ እንዳይንሸራሸር በማድረግ የደም ማነስ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

የትኞቹ ሰዎች ለደም ማነስ የበለጠ ተጠቂ ናቸው?

አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ለደም ማነስ በሽታ ተጋላጭ ናቸው። ለምሳሌ ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበትና በእርግዝና ወቅት የደም ማነስ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ በቂ አይረን፣ ማዕድንና ቫይታሚን የሌለባቸው ምግቦችን የሚያዘወትሩ አንዲሁም አንዳንድ የመድኃኒት ዓይነቶችን የሚወስዱ ሰዎች ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው።

የኩላሊት፣ የካንሰር፣ የጉበት፣ የታይሮይድ፣ የአንጀት ቁስለት ወዘተ ህመም ያለባቸው ሰዎችም በከፍተኛ ሁኔታ የደም ማነስ በሽታ ተጋላጭ ናቸው።

የተለመዱ የበሽታው ምልክቶች

• የቆዳ መገርጣት፣ የደረት ህመም፣ ራስ ምታት፣ የራስ ማዞር፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ፈጣን ወይም ስልተምቱ የሚለዋወጥ የልብ ምት፣ የድካም ስሜት እንዲሁም የእጅና እግር መቀዝቀዝ ናቸው።

መፍትሄዎች

መለስተኛ የደም ማነስ በሽታ ላለባቸው ሰዎች ሰውነታቸው በቂ ቀይ የደም ህዋስ ለማምረት የሚያግዝ የአይረን ንጥረ ነገር እንክብሎችና ቫይታሚኖች መውሰድ ጥሩ መፍትሄ ነው። በአይረን ንጥረ ነገር የበለጸጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብም ለችግሩ ቀላል መፍትሄ ነው።

የደም ማነስ በሽታው ዓይነት ከፍተኛ ከሆነ ግን ሀኪም ዘንድ በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራና የህክምና መፍትሄዎችን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል። ጤና ይስጥልን!!

ምንጭ፡-
– National Heart, Lung and Blood Institute (NIH)
– American Society of hematology
– Medical News Today

በቴዎድሮስ ሳህለ