የደሴ ከተማ አስተዳደር ህወሓትን ለመደምሰስ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገለጸ

ነሐሴ 08/2013(ዋልታ) – አሸባሪው ትህነግን ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ትግል በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አበበ ገብረ መስቀል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖችን የሚቀበሉ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።
ለተፈናቀሉ ወገኖች ስምንት መጠለያ ጣቢያ መዘጋጀቱንም ተናግረው ለተፈናቃዮችም ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በከተማዋ 55 ሺህ የሚገመት ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውንም የገለጹት ከንቲባው የከተማዋ ማኅበረሰብ ለተፈናቃዮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወሎ የመተሳሰብና የፍቅር ሀገር መሆኑን አስመስክረዋልም ነው ያሉ ሲሆን ለተፈናቃዮች ድጋፍ የማድረጉ ሥራም ይቀጥላል ብለዋል።
የከተማዋን ሰላም አስጠብቆ ለመዝለቅ ልዩ ልዩ ተግባራት መከናወኑን ገልጸው ከንቲባው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን እኩይ ድርጊት ለመቀልበስ አደረጃጀት ተሠርቷል ብለዋል።
የከተማዋን ደኅንነት የሚጠብቅ ተጠባባቂ ኃይል ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል።
የከተማዋ ወጣት ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠሩ ነው ተብሏል።
ወጣቶች ፀጉረ ልውጥን በመቆጣጠርና ኬላዎችን በመጠበቅ እየሠሩ ሲሆን በከተማዋ የተጣለው የሰዓት ገደብ ፀጉረ ልውጦችን ለመያዝ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳዳሩ የጸጥታ፣ የሀብት አሰባሳቢ እና ሌሎች ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየሠሩ መሆናቸውም ተናግረዋል።

ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ከንቲባ አበበ፡፡

በከተማዋ በአይነትም በገንዘብም 50 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ገልጸዋል። የከተማዋ መሪዎችም በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሠሩ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።