የደቡብ፣ ሲዳማና ጋምቤላ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት የሕዳሴ ግድቡን ቀጣና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ

የደቡብ፣ ሲዳማና ጋምቤላ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት

ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ከልማት ጋር የተሳሰረችበትን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ግዳጃቸውን ለመወጣት ቁርጠኞች መሆናቸውን የደቡብ፣ ሲዳማ እና የጋምቤላ ክልሎች ልዩ ኃይል አመራርና አባላት ገለጹ።

ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው በመተከል ዞን የሕዳሴ ግድብ ቀጣና ግዳጅ ለመወጣት ለመጡ የክልሎቹ ልዩ ኃይል አመራርና አባላት የስራ ስምሪትና መመሪያ ተሰጥቷል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ በተወሰደው የሠላም ማረጋጋት እርምጃ በቀጣናው ሠላም መስፈኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ሲፈጠር የነበረውን ሞትና መፈናቀል በማስቆም ታጥቀው ጫካ ገብተው ለነበሩ ታጣቂዎች የሠላም ተሃድሶ ስልጠና መስጠቱንና ከቀያቸው ተፈናቃዮችን ወደ የወረዳቸው መመለስ መቻሉንም አስረድተዋል።

ቀጣይ ግዳጆች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግና ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ቀድሞ ማክሸፍ መሆኑን ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ገልጸዋል።

የልዩ ኃይል አባላቱ በየክልላቸው ያከናወኑትን የሠላምና ማረጋጋት ስራ በመተከል ዞን ለመድገም ግዳጅ ተቀብለው ወደ ቀጣናው በመምጣታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣናው የሚገኘው የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ እንዲወጡም አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ የልዩ ኃይል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮሚሽነር አለማየሁ ባውዲ “ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ ከልማት ጋር ቀለበት ያሰረችበትን የሕዳሴ ግድብ ቀጣና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተገኘው እድል ያኮራል” ብለዋል።

የልዩ ኃይል አባላቱ የክልሎቻቸውን ሕዝብ በማሳተፍ በሠላምና ደህንነት ስራዎች ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮርዳክ ልዩ ኃይል አባላቱ የተቀበሉትን አገራዊ ተልዕኮ በሙሉ ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የሚፈጽሟቸውን ትንኮሳዎች ሲያከሽፍ የቆየ ጀግና ኃይል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁን በተሰለፈበት ቀጣና የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የአገርን ሉዓላዊነትና የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የቀደመ ልምዱ እንደሚያግዘው አመላክተዋል።

የልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው፣ በቀጣናው ማንኛውም ጸረ ሠላም ኃይል ለመፈጸም የሚያስበውን እኩይ ዓላማ ለመመከት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህነንትና ሠላም ለማስጠበቅ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የተሰጣቸው ግዳጅ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ያካተተ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው በአሸናፊነት ለመውጣት እንደሚተጉ መናገራቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።