የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው

ጃኮብ ዙማ

ሰኔ 22/2013 (ዋልታ) – የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመተላለፍ የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው።

ትዕዛዙን ያስተላለፈው የአገሪቱ ከፍተኛው የህገ መንግሥት ፍርድ ቤት ሲሆን፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ጥሰዋል በሚልም ነው ቅጣቱ የተጣለባቸው።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት በስልጣን በነበሩበት ወቅት የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን በሙስና ያቀረበባቸውን ውንጀላ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ቢጠየቁም ችሎት ባለመገኘት ትዕዛዝ መጣሳቸው ተመልክቷል። ከሶስት አመት በፊት ከስልጣናቸው የተነሱት ዙማ የሙስና ክስ ቀርቦባቸዋል።

ዙማ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ብልጹግ የሚባሉትን ቢሊየነሮቹን የጉብታ ቤተሰብ አባላት የደቡብ አፍሪካን ሀብት እንዲቀራመቱ አድርገዋል የሚሉ ይገኙበታል።

የጉብታ ቤተሰብ በደቡብ አፍሪካ ፖሊሲ እንዲቀየር፣ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር እስከማድረግ ተጽእኖ ነበራቸው፤ ይህም የሆነው በዙማ ምክንያት ነው ተብሏል።

ጃኮብ ዙማ በህገ መንግሥቱ ፍርድ ቤት በአንድ ችሎት ቢገኙም ከዚያ በኋላ ግን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በመተላለፍ በእምቢተኝነታቸው መቀጠላቸው ተገልጿል።

ኮሚሽኑን በበላይነት የሚመሩት ዳኛ ሬይመንድ ዞንዶ ህገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ቢያስተላልፍም የዙማ መታሰር ግልፅ አይደለም ነው የተባለው።

በተያያዘ ዜና በባለፈው ወር ዙማ በሙስና ክስ በቀረበባቸው ወንጀል ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።

ይህ ክስ በ1990ዎቹ የተደረገ የ5 ቢሊየን ዶላር መሳሪያ ሽያጭ ጋር የተገናኘ እንደሆነም ተጠቅሷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።