የደቡብ ክልል ለ1 ሺሕ 580 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

ሚያዝያ 23/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል የኢድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺሕ 580 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሶፎኒያስ ደስታ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት 1ሺሕ 443 ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1ሺሕ 580 ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።

በይቅርታ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 157/2007 እንዲሁም በደንብ ቁጥር 141/2008 እና በመመሪያ ቁጥር 6/2008 መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰጠው ይቅርታ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም 1ሺሕ 502 ወንዶች እና  78 ሴቶች የይቅርታው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከነዚህ ውስጥ ከእድሜ ልክ እስራት ወደ 25 ዓመት ዝቅ የተደረገላቸው 13 ወንዶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በተፈረደባቸው ወንጀል ግማሽ የታሰሩ እንዲሁም የፍርድ ጊዜያቸውን በሁለት ሦስተኛ ያጠናቀቁ፣ በማረሚያ ቆይታቸው በሥነ ምግባራቸው የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ የይቅርታው ተጠቃሚ መሆናቸውንም ኃላፊው አስረድተዋል።

እርቅ ፈጽመው ካሳ የከፈሉና በጥፋታቸው የተጸጸቱ እንዲሁም የጎዱትን ማኅበረሰብ ለመካስ የተዘጋጁትም ያካትታል ማለታቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።