የደቡብ ክልል የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ዓመታዊ ጉባኤ እና የንቅናቄ መድረክ እያካሔደ ነው

ነሃሴ 18/2013(ዋልታ) – በከተማ የመሬት አስተዳደር የሊዝ አዋጁን መሠረት ተደርጎ አየተሰሩ ያሉ ስራዎች ቢኖሩም መሬቱን በሚፈለገው ደረጃ አልምቶ ለተጠቃሚው በማቅረብ በኩል አሁንም ያልተሻገሩ ችግሮች መኖራቸውን የደቡብ ክልል የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ክልል አቀፍ ዓመታዊ ጉባኤ እና የንቅናቄ መድረክ እያካሔደ ሲሆን በመድረኩ ላይ የክልሉ የ2013 ዓ.ም የበጀት አመት የስራ አፈፃፀም በመገምገም የ2014 ዓ.ም የበጀት ዓመት የስራ አቅጣጫ ያስቀምጥበታል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የደቡብ ክልል የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፉ አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንደገለፁት በሊዝ አዋጁ መሠረት በከተማ ለልማት የሚውሉ መሬቶችን መለየት  ስራ   ወሳኝ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም በሁሉም ከተሞች አካባቢ አፈፃፀሙ ላይ አሁንም ውስንነት ተስተውሏል ብለዋል። በዘርፉ የታዩ የሌብነት እና ህገወጥ የሆኑ አሰራሮች አሁንም ክልሉ ያልተሻገራቸው ዋንኛ ችግር መሆኑን ነው የገለፁት።

ህገወጥ የመሬት አጠቃቀም እና ከዘርፉ ጋር ተያይዘው ሲስተዋሉ የነበሩ ስር የሰደዱ ችግሮች አሁንም ቀጥሏል ሲሉ የቢሮው ሀላፊ ይህም ችግር በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ላይ በሁሉም ቦታ ይታያል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ በራሱ ይዟቸው የሚመጣ ችግሮች መኖሩን ያነሱት አቶ ተስፋዬ እያደገ የመጣውን የከተማ ነዋሪ የቤት ፍላጎት ለሟሟላት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ትልቅ ፈተና እንዲጋረጥበት ማድረጉን አንስተዋል።

መንግስት የከተሞች በፍጥነት ማደግን ተከትሎ የመጣውን የከተማ ነዋሪ ቁጥር ያማከለ የቤት ፍላጎት በተለያዩ የቤት ፈላጊ ፍላጎት መሠረት ለቤት ልማት ሊውሉ የሚችሉ መሬት ለማቅረብ እቅድ ነድፎ እየሰራ ይገኛል። የቤት ልማቱን ፍላጎት ለሟሟላት መሬት በማዘጋጀት እና አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን በሟሟላት ሁሉንም የቤት ልማት አማራጮችን በመጠቀም ለመሠራት እየተንቀሳቀሰ ቢገኝም ተገቢውን የአመራር ትኩረት አለማገኝቱ ነው በዚህ መድረክ ላይ የተነሳው።

በተለይም በማህበር በመደራጀት እና በተለያዩ አማራጭ ቤት የማልማት ፍላጎትና አቅም ያላቸው አካላት መሬቱን በህግ አግባብ የማግኘታቸው ሁኔታ ላይ ክፍተት ተስተውሏል እንደ ቢሮው ሀላፊ ገለፃ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰፊ ክፍተት እየተስተዋለበት የሚገኘው እና ህዝብ ጥያቄ እያነሳበት የሚገኝ ዘርፍ ነው የተባለው የመንግስት ፕሮጀክቶች ግንባታ ናቸው። የመንግስት የከተማ ፕሮጀክቶች ግንባታ ምንም እንኳ አብዛኞቻቸው በተያዘላቸው የግዜ ገደብ፣ ጥራት እና ወጭ እየተከናወኑ የሚገኙ ቢሆኑም በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ከዚህ ውጭ ግንባታቸው እየተከናወኑ እንደሚገኙ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል።

አሁን እየታየ ያለው ፈጣን የከተሞች እድገት እያደገ የመጣውን የከተሜውን ነዋሪ በትክክል ያማከለ ከፍተኛ የመንግስት መዋለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የከተሞች መሠረተ ልማት በአግባቡ ተመርተው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት በመስጠት  እንደ ሀገር የተጀመረውን ሀገራዊ ብልፅግናን ማምጣት ወደሚችሉበት ጎዳና እንዲሄዱ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት ተስፋዬ ይገዙ አሳስበዋል።

በትናንትናው እለት በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የተጀመረው ክልል አቀፍ ጉባኤ እና የንቅናቄ መድረክ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በመድረኩ ላይ የክልሉ ሁሉም ከተሞች የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሴክቶሪያል የስራ አመራሮች የበጀት ዓመቱን የስራ አፈፃፀም በማዳጥ ይገመግማሉ። በመቀጠልም የ2014 የትኩረት አቅጣጫን በማስቀመጥ የተሻለ የስራ አፈፃፀም የሚከናወንበትንሁኔታ እንደሚያስቀምጡ ተጠቁሟል።

(በሚልኪያስ አዱኛ)