የደቡብ ጎንደር ዞን ሕዝባዊ ሰራዊት የቀረበለትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር ዘመተ

ጥቅምት 26/2014 (ዋልታ) ከመንግሥት ለቀረበለት የሽብር ቡድኑን ሕወሓት ወረራ ቀልብሶ ቡድኑን የማጥፋት ክተት አዋጅ ፈጣን ምላሽ ከሰጡት ውስጥ የሆነው የደቡብ ጎንደር ዞን ሕዝባዊ ሰራዊት ወደ ግንባር ዘመተ፡፡

ሕዝባዊ ሠራዊቱ የአማራ ሕዝብን አዋርዶ፣ ዘርፎና ገድሎ ኢትዮጵያን ለመበታተን የተነሳውን አሸባሪው ሕወሓት ግብአተ መሬት ሳይፈጽም ላይመለስም ተማምሎ ወደ ግንባር አቅንቷል።

የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ የኅልውና ዘመቻው የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እስከመጨረሻ ነፃ ለማውጣት እንደሆነ አብራርተዋል። ኃላፊው እንዳሉት ጠላትን ማጥፋት የዘመቻው መዳረሻ ነው።

አሚኮ እንደዘገበው በሁሉም ግንባሮች ጠላት ዳግም በማያንሰራራበት ደረጃ ለመምታት ዝግጅት መደረጉን በመግለጽም መንግሥት ለዘማቾች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ቀለመወርቅ ምህረቴ በበኩላቸው ዘማቾች ታሪክ እየሰሩ ካሉት የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የፋኖ፣ የሚሊሻ አባላት እና የአማራ ሕዝብ ጋር ተሰልፈው ተልዕኳቸውን በጀግንነት እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።