የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎቻችን በከፍተኛ ጫና ውስጥ ናቸው – ኩመራ ዋቅጅራ

የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ

ሰኔ 7/2016 (አዲስ ዋልታ) የዱር እንስሳት ጥብቅ ቦታዎቻችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት በከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣኑ የተፈጥሮ ሃብታችን ለሀገር እያበረከተ ያለውን ፋይዳ ለማስጠበቅ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እያከናወናቸው ስላለው ተግባራትና ያስመዘገባቸውን ውጤቶች እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብታችን ላይ የተጋረጡ ችግሮችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳት በሰው ሰራሽ ምክንያት በተለይም ህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ ቦታ መስፋፋት፣ በሰፈራና የግንባታ ስራዎች በመሳሰሉት ምክንያት በእንስሳት ጥብቅ ስፍራዎች ላይ ጫናዎች የእበዙ መጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ስለዱር  እንስሳት ሀብታችን በህብረተሰቡ እና በሚዲያዎች ጭምር የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን አስታውሰው ይህ ችግር በተከታታይ መረጃ በመስጠትና ግንዛቤ በመፍጠር መቀረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የመረጃ ክፍተትንና የግንዛቤ መዛባትን  ለመቅረፍ ከመገናኛ ብዙኃንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአገራችን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ከዓለም ቀደም ብላ በተግባር መጀመሯን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ  በ15ኛው ክፍለ ዘመን የሱባ ደንን በኋላም በ17ኛው ክፍለ ዘመን የመንዝ ጓሳ የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራ በማህበረሰብ አነሳሽነት እንደተጀመረ  አውስተው ዓለም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የጀመረው በኢንዱስትሪ አቢዮት ዘመን ነበር ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በ1909 በህግ ደረጃ ዝሆን እንዳይታደን አገራችን አዋጅ አውጥታ እንደነበርና የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ በአገራችን የቆየ ተግባር እንጂ ከቅኝ ግዛት ጋር እንደማይያያዝ አስገንዝበዋል።

በብሔራዊ ፓርኮች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የእሳት ቃጠሎን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ እንደ ቃፍታ ሽራሮ፣ ሰሜንና ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች የእሳት አደጋ ለመቀነስና መከላከል የእሳት አደጋ ብርጌድ መቋቋሙን እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓት መሟላቱን ተናግረዋል። ወደፊትም አስቀድሞ የመከላከልና የአቅም ግንባታ ስትራቴጅን ተግባራዊ እንደሚደረግ አንስተዋል።

የብዝሃ ህይወት መጥፋት፣ ብክትና የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን በእጅጉ እያሳሰበው ነው ያሉት አቶ ኩመራ እንደ ኢትየጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት በችግሩ ከፍተኛ ተጎጂ መሆናቸውን አብራርተው ይህን ለመቀነስ አገራችን የ2015 የፓሪስ ስምምነትን፣ የ2022 የሞንትሪያል የብዝሃ ህይወት ማዕቀፍን፣ የዘላቂ የልማት ግቦች እና ተፈጥሮ መሰረት ያደረገ መፍትሄ ኢኒሸቲቭን ፈርማ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።

 

በቴዎድሮስ ሳህለ