የዲያስፖራ አባላት በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡትን ገንዘብ ወደ ሌላ የግለሰብ አካውንት እንዲገባ ያደረጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) የዲያስፖራ አባላት ሀገራዊ ጥሪውን መሰረት በማድረግ በጦርነቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል ያሰባሰቡትን ገንዘብ በማጭበርበር ወደ ሌላ የግለሰብ አካውንት እንዲገባ ያደረጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለፀ።
በአሜሪካ እና በጀርመን ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከራሳቸው፣ ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ያሰባሰቡትን የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በማጭበርበር የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ተብሏል፡፡
የዲያስፖራ አባላቱ ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ለገሀር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲያስፖራ ቅርንጫፍ ያሰባሰቡትን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ሲሞክሩ የባንኩ ሰራተኞች በተባለው አካውንት ያስገቡ በማስመሰል ወደ ሌላ ግለሰብ አካውንት ገቢ ካደረጉ በኋላ ይህንኑን ደረሰኝ ለዲያስፖራ አባላቱ ሰጥተዋል።
በዚህ መሰረት የዲያስፖራ አባላቱ ገንዘቡ ገቢ የተደረገው ወደ ግለሰብ አካውንት መሆኑን በማረጋገጣቸው ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውንና ፖሊስም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የወንጀል ምርመራ ቢሮው ገልጿል፡፡
በተያያዘም በሌሎች ባንኮች በተመሳሳይ እየተፈፀሙ ያሉ ወንጀሎችን እያጣራ እንደሚገኝም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ አመልክቷል።