የዲጅታል ፋይናንሺያል ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል ውይይት ተካሄደ


ግንቦት 24/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከግል ባንኮች ፕሬዝዳንቶች ጋር የዲጂታል ፋይናንሺያል ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ያለመ ውይይት አካሂዷል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ላይ እንዳሉት ከባንኮች ጋር ተያይዘው የሚፈፀሙ የሳይበር፣ የሞባይል ባንኪንግ እና ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየተወሳሰቡና እየተበራከቱ መምጣታቸውን አስገንዝበዋል፡፡

የዛሬው መድረክም ይህን በመገንዘብ በጋራ በመምከር ወንጀሉን ለመከላከልና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ አቅም እያደገ ሲሄድ በዚያው ልክ ችግሩም አብሮ እንደሚያድግ ታሳቢ መደረግ እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ሲበለጽግ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተለይቶ ለደንባኞች፣ ለባንክ ሠራተኞች እና ለሕግ አስከባሪው ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡

ቴክኖሎጂ ሲበለጽግ ፖሊስ ከባንኮች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት መረጃ የሚያገኝበትና የሚሰጥበት አሰራር እንዲዘረጋም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ በበኩላቸው ዲጂታል ፋይናንሺያል ላይ የሚስተዋለው ወንጀል የሰፋና የገዘፈ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ለችግሩ መፍትሄ ማስቀመጥ እንጂ ከዲጂታል ፋይናንስ ሲስተም ውጭ መሆን እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ

የዲጅታል ፋይናንስ ወንጀልን ለመከላከልም ቴክኖሎጂ፣ የህግ ማዕቀፍ፣ ትብብርና የማህበረሰብ ንቃት ላይ የሚሰራው ስራ ችግሩን እንደሚያቃልለው ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ብሄራዊ መታወቂያ መጠቀም እንደ አንድ የችግሩ ማቅለያ መፍትሄ ነው ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ሙሊሳ አብዲሳ በሞባይል ባንኪንግና በሶሻል ሚዲያ አማካኝነት በሚፈፀሙ ወንጀሎች ዙሪያ የጥናት ሰነድ አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በራሱ ተነሳሽነት ወስዶ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎችና ተወካዮች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥና በየደረጃው ያሉ የምርመራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በቀጣይም በውይይቱ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን አፈፃፀም ለመገምገም የጋራ ውይይት ፎረሙ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሷል።