ጥር 20/2014 (ዋልታ) የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ጉዳት የደረሠባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመገንባት ቃል መግባቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዳሉት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በክልሎቹ ጉዳት የደረሰባቸውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ መልኩ ለመገንባት ቃል ገብቷል።
ትረስት ፈንዱ ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ 3 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርግና ግንባታውም ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ይወስዳል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በተሻለ ጥራትና ደረጃ እንደሚገነቡ ገልጸው ይህም የትምህርት ጥራትን ለማስፈን የጎላ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡