የዳያስፖራ አባላት ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ነው

ግንቦት 22/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የተዘጋጁት “ኤች አር 6600” እና “ኤስ 3199” የተሰኙ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን በአሜሪካ የሚኖሩ አንድ የዳያስፖራ አባል ተናገሩ።

ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ መሆኑን በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዳኛቸው ተሾመ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን “ዊ ካን” እና “ኤፓክ” የተሰኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስብስቦችን በማቋቋም በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማስረዳት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

ሕጎቹ በአገርና ሕዝብ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በማስረዳት ለኮንግረስና ለሴኔት አባላቶች የማግባባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር በሚካሄደው የመካከለኛ ጊዜ ምርጫ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ በድምጻቸው ጫና ለማሳደር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሜሪካን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የምርጫ ድምጻቸውን በመጠቀም የባይደን አስተዳደር ሕጎቹን እንዳያጸድቅ ጫና ማሳደር እድል እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ እነዚህ ሕጎች እንዲጸድቁ ፍላጎት ያላቸው የሴኔት አባላት በምክር ቤቱ ከፍተኛ ድምጽ እንዳያገኙ የማድረግ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሕጎችን እንዳያወጣና የሚደረገውን ያልተገባ ጫና መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ ሲፈጽመው የነበረውን ድርጊት ተቃውሞ በማሰማት አንድ የኮንግረንስ አባል ድርጊቱን እንድታወግዝ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን ለማስቀረት ዳያስፖራው አሁንም ከፍተኛ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም እንዳለው ኩነቱ አመላካች መሆኑን ነው ያነሱት።
“ኤች አር 6600” እና “ኤስ 3199” የተሰኙ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ መንግሥትም የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጥረቶች እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።