የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ህልፈት

ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም መለየቱ ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ገናና ስም ካላቸው መካከል አንዱና ተወዳጁ ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ነሐሴ 27/2013 እኩለ ሌሊት በድንገት ማረፉን ወዳጆቹ አሳውቀዋል።

በ1955 በፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ ውስጥ የሙዚቃ ህይወቱን የጀመረው አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ በወቅቱ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ‘ኤልቪስ ፕሪስሊ’ የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶት ነበር።

“ተማር ልጄ” በሚለው አይረሴ ዘፈኑ በብዙዎች ልብ ውስጥ የገባውን ድምፃዊው ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ የኪነ ጥበብ ቤቱ ብሔራዊ ቴአትርን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያን አድናቂዎቹ ሀዘናቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፆች እየገለፁ ይገኛል።

ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት በድምፃዊው ህልፈት ሀዘኑን አየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ ሁሉ መፅናናትን ይመኛል።