ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሳይቋረጥ ያለአንዳች የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የምዕራብ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር አደሬ ቶላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፖሊስ ምርጫው ከመካሄዱ አስቀድሞ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው፣ ህዝብና የፀጥታ ሀይሉ የሚጠበቅበትን በማድረጉ ምርጫው በሰላም ሊጠናቀቅ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ኦነግ ሸኔ በዞኑ በሚገኙ ሚዳ ቀኝ፣ በሊበን ጃዌ ስር በምትገኝ አገል ጎቦ ቀበሌ፣ ድሬ ጭኔ እና አደበር በተባሉ ወረዳዎች ላይ ከሩቅ ስፍራ ተኩስ በመክፈት ህዝብ የፀጥታ ችግር አለ ብሎ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይሄድ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም፣ ህዝቡ ከርቀት ሲሰማ በነበረው ተኩስ ሳይረበሽ በምርጫ ጣቢያዎች ተገኝቶ ድምፁን ሲሰጥ እንደነበር ገልፀዋል።
በዚህም ህዝባችን ለሰላምና ልማት ያለውን ቁርጠኝነት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አሳይቷል ብለዋል።
የፀጥታ ሀይሉም የፀጥታ ስጋት በተስተዋለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በፍጥነት ደርሶ ምርጫው ሳይቋረጥ ማስቀጠል መቻሉንና በዞኑ በሚገኙ 20 ወረዳዎች ስር ያሉ ምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ያለምንም ስጋት ድምፅ እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉ ነው የተገለፀው፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በምዕራብ ሸዋ ዞን አንድ ምርጫ ጣቢያ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር መግለፃቸውን አስታውሰው፣ የፀጥታ ሀይሉ በፍጥነት ችግሩ በተስተዋለበት ስፍራ ለተፈጠሩ ስጋቶች ምላሽ በመስጠት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ማስቀጠል እንደቻለ ኮማንደር አደሬ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር ተቀናጅቶ በምርጫው የተቃጡ ሙከራዎችን እንዳከሸፈ ሁሉ ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል የጠላትን እኩይ ተግባር በማክሸፍ ሂደት ተሳትፎን ማጠናክር እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
(ደረሰ አማረ)