የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ቤት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ለ2015 በጀት አመት 5 ቢሊዮን 138 ሚሊዮን 454 ሺሕ ብር በጀት በማፅደቅ እና ሹመት በመስጠት ጉባኤውን አጠናቋል።

ምክር ቤቱ በ1ኛ አመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤው የድሬዳዋ መተዳደሪያ ቻርተር ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቷል።

ለምክር ቤቱ የበጀት ድልድሉን ያቀረቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሱልጣን አሊይ እንዳሉት ከታቀደው በጀት ውስጥ የፌደራል መንግስት 1 ቢሊዮን 936 ሚሊዮን 889 ሺሕ ብር የበጀት ድጎማ አድርጓል።

የቀረው ከአስተዳደሩ ከሚሰበሰበው ገቢ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ዘንድሮ የታቀደው በጀት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ907 ሚሊዮን ብር ወይም በ21በመቶ ጭማሪ አለው ብለዋል።

ከተመደበው በጀት ውስጥ 2 ቢሊዮን 484 ሚሊዮን ብር የሕዝብን መሠረታዊ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለሚያቃልሉ ነባር የካፒታል ፕሮጀክቶች የተመደበ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ ዘንድሮ በገጠር እና በከተማ ቀደም ሲል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ በመረባረብ መሠረታዊ ውጤት ለማምጣት አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ የስራ አጥ ምጣኔ በመቀነስ ረገድ አበርክቶ እንደሚኖራቸውም አንስተዋል።

ከፌዴራል መንግሥት ድጎማ እና ከአስተዳደሩ ከሚገኘው በጀት በተጨማሪም 561 ነጥብ 1ሚሊየን ብር በጀት ከልማት አጋር አካላት ለአስተዳደሩ ፈሰስ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበጀት ድልድሉ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኃላ በአንድ ድምፀ ታቅቦ በጀቱን ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።

ከበጀት ማፅደቅ በተጨማሪ ምክር ቤቱ የድሬዳዋ መተዳደሪያ ቻርተርን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት በማድረግ መሠረታዊ ግብአቶች አሰባስቧል።

ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ ለኢፌዴሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚላክ መሆኑ ተመልክቷል ።

በመጨረሻም ከሪማ አሊ እና መርቆስ ባዩ የድሬደዋ አስተዳደር የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በተጓደሉት አባላት ምትክ በመሾም የሁለት ቀናት ጉባኤውን አጠናቋል ።