የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት የሀገርን ህልውናን ለመታደግ ዝግጁ ነን አሉ

ነሃሴ 10/2013(ዋልታ) አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር ማንኛውንም መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችና አመራሮች አስታወቁ።

ሠራተኞቹና አመራሮቹ ትናንት ደም የለገሱ ሲሆን፣ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሠራዊቱ ድጋፍ እንዲውል ወስነዋል፡፡

በድጋፍ አሰጣጡ ሥነ- ሥርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ፥ አሸባሪው የህውሃት ቡድን ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር የቃጣውን ጥቃት በተባበረ አንድነት መመከት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሠራዊቱ የጀመረውን ተልዕኮ ለማሳካት በዕውቀቱ፣ ገንዘቡና ጉልበቱ በመደገፍ ማንኛውንም  መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን  አስታውቀዋል፡፡

ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱ የሚገኙት ጫና ለመመከት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ተቋማት እውነቱን እንዲገነዘብ ማድረግ ይጠበቅብናል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሣይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሱራፌል ጌታሁን ናቸው።

ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ደመወዝ መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ ካስፈለገም ግንባር ድረስ በመዝመት መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ሠራተኛ አቶ አደም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ሀገርን ለማፍረስ የሚጣጣረውን አሸባሪው የትህነግ ርዝራዥ ለመደምሰስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።

”ደም ለግሰናል፣ የወር ደመወዛችንን ለሀገር መከላከያ አበርክተናል፤ እኛም ግንባር መጓዝ ካለብን ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎችና ሠራተኞችም ሀገር አፍራሹን ቡድን ለመደምሰስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ለመወጣት ስንቅ በማዘጋጀት ፣ ገንዘብ በማዋጣትና ደም በመለገስ  ላይ እንደሚገኙም ኢዜአ ዘግቧል።