የድንጋይ ከሰል ማዕድንን በሀገር ውስጥ በማምረት 200 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳኑን ባለስልጣኑ አስታወቀ

ነሃሴ 03/2013 (ዋልታ) – የድንጋይ ከሰል ማዕድን በሀገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግ 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማዳኑን የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ መገርሳ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ክልሉ ከውጭ ሀገር በከፊል የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ማዕድን በሀገር ውስጥ ለመተካት ሲሰራ ቆይቷል።

በዘንድሮ በጀት ዓመትም በተለይ በጅማ ዞን አካባቢ ማዕድኑን በስፋት ማምረት መጀመሩን ያስታወቁት አቶ ተስፋዬ ፣በዚህም ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሊወጣ ይችል የነበረውን 200 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በጅማ ዞን በተለይ በጊቤ ተፋሰስ አካባቢ የድንጋይ ከሰል የማምረት ስራው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ያመለከቱት አቶ ተስፋዬ ፣ በዞኑ ከሃምሳ በላይ የተደራጁ ማህበራት ከባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በክልሉ በማዕድን ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ከተፈጠረው 86 ሺ የስራ እድል ውስጥ ወደ 40 ሺ የሚጠጋው በድንጋይ ከሰል ማምረት ስራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአመራረቱን ጥራት ለማሳደግ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎች በአካባቢው ላይ እንዲገነቡ በማድረግ የድንጋይ ከሰል ማዕድኑ ታጥቦ ለገበያ እንዲቀርብ እየተረገ መሆኑንም አመልክተዋል።