የጅቡቲው ኩባንያ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) ”ኢንፔክስ ሶሉሽንስ ፍሪ ዞን” የተሰኘ የጅቡቲ ኩባንያ በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መዋዕለ ነዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና አመራሮች ከ”ኢንፔክስ ሶሉሽንስ” የስራ ሀላፊዎች ጋር በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ዙርያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በንግድ ቀጠናው ያሉ አገልግሎቶች፣ የተቋቋሙበት አላማና ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ በኩል ለኩባንያው ገለፃ ተደርጓል፡፡
ኩባንያው በበኩሉ የስራ እንቅስቃሴዎቹን፣ በዘርፉ ያካበታቸውን ልምዶች እንዲሁም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ኩባንያው ለማከናወን ስላሰበው ኢንቨስትመንት ዝርዝር ማብራሪያ አቅርቧል፡፡
በቀጣይም “ኢንፔክስ ሶሉሽንስ ኩባንያ ፍሪ ዞን” በነፃ ንግድ ቀጠናው ኢንቨስትመንቱን ለመጀመር የሚያስችለውን የፕሮጀክት ጥናት ለኮርፖሬሽኑ በማቅረብ ምላሽ ይሰጣል ተብሏል፡፡
ሁለቱ አካላት በቀረቡ ፅሁፎችና መወያያ ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በንግድ ቀጠናው ያሉ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶችን መጎብኘታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡