የጅቡቲ ልዑክ በኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የጋራ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገባ

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) የጅቡቲ ልዑክ በኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች ኮሚሽን የጋራ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ መግባቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ልዑኩ አዲስ አበባ ሲገባ በከፍተኛ የመንግስት አመራሮች አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሦስት ዓመታት ያህል ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያና የጅቡቲ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ከጥቅምት 15 እስከ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ስብሰባው በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው ሁለንተናዊ ግንኙነት ዙሪያ የሚመክር ሲሆን በተለይ በትራንስፖርት፣ በንግድ፣ በፋይናንስ፣ በሎጂስቲክስ፣ በሰዎች ዝውውር፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
ትናንት እና ከትናንት በስትያ ውሎው ኮሚሽኑ ባቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ አማካኝነት ከዚህ ቀደም ስምምነት የተደረሰባቸውንና አሁን መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች ከተወያየ በኋላ፣ ውሳኔ ሊደረስባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን የለየ ሲሆን ዛሬ ሚኒስትሮች በተገኙበት በሚደረገው የመዝጊያ ስብሰባ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ይጠበቃል።