ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች የአሸባሪው አልሻባብን ተግባር የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በዛሬው ዕለት አካሂደዋል።
ነዋሪዎቹ አልሻባብ ድንበር አልፎ በአፍዴር እና ሸበሌ ዞኖች ጠረፋማ መንደሮች ነዋሪ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ተግባር በጥብቅ እንደሚያወግዙ እና በሽብር ቡድኑ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በመደገፍ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
ሰልፈኞቹ “የሽብር ቡድኑን እኩይ ዓላማ እናወግዛለን”፣ “ሰላማችን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብረን እንሠራለን”፣ “የአሸባሪዎች ጥቃት ከልማታችን አይገታንም”፣ “ልማታችንን እናፋጥናለን” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋል።
የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር መሐመድ አሊ የአልሸባብን የሽብር ተግባር ለመከላከል ሕዝቡ በንቃት አካባቢውን በመጠበቅ እና በመከታተል አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥም ለፀጥታ አካላት ጥቆማ ማቅረብ እንዳለበት አመልክተዋል።
የክልሉ መንግሥት የጥፋት ተልዕኮዎችን ለማክሸፍ ለሚያደርገው ጥረት ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ጥሪ ማቅረባቸውን አና ሰልፈኞቹም ለጸጥታ ኃይሎች የደም ልገሳ ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።