የገቢዎች ሚኒስቴር በወላይታ ሶዶ ከተማ በእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የገቢዎች ሚኒስቴር በወላይታ ሶዶ ከተማ በመርካቶ የገበያ ማዕከል በእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ40 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለውን የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ድጋፉን ለወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ለዶክተር እንድሪያስ ጌታ አስረክበዋል፡፡

አቶ ላቀ በዚሁ ወቅት የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ገቢ ከመሰብሰብ በተጓዳኝ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ተጎጂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ አብይ ተግባራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በወላይታ ሶዶ ከተማ በመርካቶ የገበያ ማዕከል በደረሰው አደጋ ተጎጂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በአገሪቱ በኮንትሮባንድ የሚያዙ ቁሳቁስ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ተጎጂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸውበወላይታ ሶዶ ከተማ የደረሰው አደጋ አስከፊ መሆኑን ተናግረው ተጎጂዎችን ለማቋቋም በክልልና በዞን ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የጉምሩክ ኮሚሽን ተጎጂዎችን ለማቋቋም ላደረጉት ድጋፍም በክልሉ ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደገለፁት ድጋፉ የለውጡ መንግሥት ለዜጎች የሰጠውን ትኩረት ያሳያል፡፡

ድጋፉ የምግብ ዘይት፣ ስኳር አልባሳት እና መሠል ቁሳቁስን እንደሚያካትት ከደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።