ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የገቢዎች ሚኒስቴር ከሃምሌ 03 እስከ 09/2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ባከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ከ50 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች እንደተያዙ አስታወቀ፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹ ከሀገር ሊወጡ እና ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ናቸው።
የገቢ ኮንትሮባንድ 47 ሚሊየን 535 ሺህ 362 ብር፣ ወጪ ደግሞ 2 ሚሊየን 953 ሺህ 432 ብር፣ በድምሩ የ50
ሚሊየን 488 ሺህ 794 ብር ግምት አላቸው ብሏል።
ከኮንትሮባንድ ቁሶቹ መካከል የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ ወርቅ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ጫማ፣ ምግብ ነክ፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኮስሞቲክስ፣ ሲጋራ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ፣ የሰው መድኃኒት ሲሆኑ፣ 42 ተሽከርካሪዎች ደግሞ ኮንትሮባንድ ሲያዘዋውሩ መያዛቸው ታውቋል፡፡
ኮንትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ኅብረተሰቡ፣ የክልልና የፌደራል የጸጥታ አካላት እንዲሁም ሠራተኞች ከፍተኛ ሥራ ማከናወናቸው ተገልጿል።
በቀጣይም ለሀገር እድገት ኮንትሮባንድን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መጠየቁን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።