የገና በዓልን በላልይበላ ለማክበር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩ ተገለፀ

ኅዳር 29/2014 (ዋልታ) – በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ተወሮ የነበረው እና የወገን ጦር በወሰደው የተቀናጀ ርምጃ ነፃ በወጣው ላልይበላ የገና በዓልን ለማክበር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
በወረራ ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር መንግሥት ጥረት እያደረገ ነው ።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮም ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የዘንደሮውን የገና በዓል በላልይበላ ከተማ ለማክበር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጣሂር ሙሐመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በላልይበላ ከተማ ወረራ በመፈጸም በተወሰኑ ወራቶች ኢኮኖሚውን ጎድቶት ቆይቷል፤ ይህንን ለማነቃቃት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላልይበላ ከተማ ይከበራል።
በድምቀት ለሚከበረው በዓል የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን ተቀብሎ ማስተናግድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም በቦታው ተገኝተው በዓሉን እንዲያከብሩ ኃላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሚመለከታቸው ግለሰቦች እና የመንግሥት ልማት ድርጅቶችም ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአካባቢው በሽብርተኛው የሕወሓት ወራሪ ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶች ጥገና እየተደረገላቸው እንደሆነ ኃላፊው መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።