የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በትግራይ ክልል በቅርቡ የተከናወኑ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለልማት አጋሮች ቡድን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ገለጻ አደረጉ፡፡
ሚኒስትሩ መንግሥት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ለተጎዱት ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታን በማዳረስ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም የመልሶ ማቋቋሙና የሰላም ግንባታ የመንግስት ቀዳሚ ስራ እንደሆነም ነው ያብራሩት፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ አክለው የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ስራን ለማከናወን የተገደደው የዜጎች ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ ስለወደቀ መሆኑን ነው ያስታወሱት፡፡
የህግ ማስከበር ሥራው የተከናወነው ለዜጎች ደህንነት ከፍተኛ ጥንቃቄ በተደረገበት አኳኋን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሂደቱም ሰብዓዊ እና መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም ባቀረቡት ገለፃ ላይ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሰብአዊ ዕርዳታውም ሆነ መልሶ በማቋቋሙ ሂደት ላይ ከፍተኛ መሻሻሎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
እስካሁን የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታው ለ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝብ መድረሱን እስካሁን ከ305 ሺህ ኩንታል በላይ እህል መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ስርጭት በትግራይ ባሉ ሁለት ካምፖች ውስጥ ለሚኖሩ 26 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች መዳረሱን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይም የምግብ እርዳታው ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰጡር እና ጡት ለሚያጠቡ እናቶች በአስቸኳይ እንዲደርስ የልማት አጋሮች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በቀጣይ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያሻቸው ለ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ሚኒስትሩ በቅርቡ ከልማት አጋሮች በተለይም የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች በትግራይ ውስጥ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቶች እንዲደርሱ ለማስቻል ያሳዩትን ንቁ ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡
አያይዘውም የተፋጠነ የእርዳታ አቅርቦትን የበለጠ ለማሳደግ መንግስት ወደ ክልሉ እና ወደ አከባቢው የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰራተኞች እንቅስቃሴ በፍጥነት በመጨመር ዕርዳታው እንዲዳረስ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ የኢትዮጵያ መንግስት ለተጎዱ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረስ ረገድ ላሳየው አመራር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የልማት አጋሮች ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተጨማሪ ሰብዓዊ ድጋፍ ለመስጠት አሁን ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ መሻሻል እንደሚኖርባቸውና አቅርቦትን ለማቀላጠፍ ውጤታማ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የበለጠ ለማሳደግ እና የሰላም እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም መርሃግብሮች ላይ ለመስራት የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ዶክተር ካትሪን ሶዚ የልማት አጋሮች አባላት ስደተኞችን እና ሌሎች በአገሪቱ ውስጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመርዳት ኃላፊነቱን በመወጣት ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማጠቃለልም አቶ አህመድ ሺዴ የልማት አጋሮችና መንግስት በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ፈጣን ሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስ እና የመልሶ መገንባት ስራዎች በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወኑ ለማድረግ እንደሆነ በማስረዳት ሁለቱም ወገን አንድ ዓይነት ዓላማ እንዳላቸው በመናገር ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የልማት እርዳታው ቡድን 30 የሁለትዮሽ እና ሁለገብ የልማት አጋሮችን ያቀፈ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የልማት እርዳታው ቡድን ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ውይይት ማጎልበት፣ የብሔራዊ ልማት ዕቅድ እና የዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ውጤታማ አፈጻፀም፣ ክትትልና ግምገማ ማድረግ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡