የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ


ግንቦት 6/2016 (አዲስ ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ አዲሱን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል፡፡

የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ በንባብ ያቀረቡት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የረቂቅ አዋጁን መሻሻል አስፈላጊነት እና በምርመራው ሂደት የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

የአርሶና አርብቶ አደሩን እና ከፊል አርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ አገሪቱ ከደረሰችበት ዘርፈ ብዙ እድገት ጋር እኩል ለማራመድ እንዲቻል፣ የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማደራጀትና ለተጠቃሚው በአግባቡ ለማሰራጨት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ በመፍጠር መንግስት እና የመሬት ተጠቃሚዎች አስተማማኝ የሆነ መረጃ የሚያገኙበትን ዘመናዊ የመሬት መረጃ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ ነውም ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የተፈጥሮ ሃብቶችን በዘላቂነት በመጠበቅና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ የሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ማረጋገጥና አካታች ስርዓት መደንገግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ውይይት የተደረገበትና በጥልቀት የታየ መሆኑን አንስተው የአርሶ አደሩን በኪራይ ስም ከመሬት ያለመነቀል መብት፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ ጋር የተያያዙ የንብረት ባለቤትነት እና በወል የተያዘ የግጦሽና የደን መሬት አጠቃቀምን የተመለከቱ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በሰጡት ማብራሪያ የተነሱት ጥያቄዎች ትክክል መሆናቸውን አንስተው መካተት አለባቸው የተባሉትን ማካተት እንደሚቻልና ነገር ግን የአዋጁን አፈጻጸም በሚመለከት ክልሎች የራሳቸውን ህግ ስለሚያወጡ የአፈጻጸም ችግሮች እንደማይኖር ማስረዳታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አድርጎ አፅድቆታል፡፡