“የጉሚ በለል” ውይይት በህገ-ወጥ ስደት ዙሪያ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) 22ኛው ዙር “የጉሚ በለል” ውይይት የህገ-ወጥ ስደት መንስኤው፣ የሚያስከትለው ጉዳት እና መፍትሄው በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ይገኛል።

በውይይቱ በርካታ ዜጎች ህይወታችንን እንቀይራለን በሚል ወደ ተለያዩ ሀገራት በህገ-ወጥ መንገድ በመሰደድ ለስቃይ እንደሚዳረጉ ተገልጿል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የህገ-ወጥ ስደት የተበራከተበት ምክንያት ሰዎች ህይወታቸውን ለመቀየር ካላቸው ህልም የሚመነጭ ነው ብለዋል።

የህገ-ወጥ ስደት ጉዳት ያለውና በስደቱ ምክንያት ሰዎች በሞራል እንዲሁም በአካል እና የተለያዩ ኢ-ሰብዓዊ ጉዳቶች እንደሚያደርስ ጠቁመዋል።

ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት የሥራ እድሎችን በማመቻቸትና ለዜጎች በቂ ግንዛቤ  በመፍጠር ህገ-ወጥ ስደትን መቀነስ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የህገ-ወጥ ስደት መበራከት የኢኮኖሚ ችግር መሆኑን ገልጸው የሥራ እድል መፍጠር እና ዜጎች በተለይም ወጣቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያዘዋውሩ ደላሎችን በመከታተል መንግሥት እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም ተጠቅሷል።

በቡላ ነዲ