የጉምሩክ ኮሚሽን ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – የጉምሩክ ኮሚሽን እና የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታና የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና  ተፈራርመዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ንግድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ቀልጣፋና ፍትሃዊ እንዲሁም በእውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲመራ ለማስቻል እስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በሰው ሀይል ልማት፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም የጉምሩክ አሰራርን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ የሚያደርጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆንና የወጪና የገቢ ንግዱ ዘመናዊና ቀልጣፋ እንዲሆንም ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ ቅርሶች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡና ወደ ሀገር እንዳይገቡ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር፣ የወጪና የገቢ ንግድ እቃዎች እንቅስቃሴ ይበልጥ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ከኢትዮጵያ ጉምሩክ አስተላላፊዎች የሙያ ማህበር ጋር እንዲሁም በኢትዮጵያ ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን ከኢትዮጵያ ሴቶች ላኪዎች ማህበር ጋር በጋራ ለመስራት የስምምነት ሰነድ መፈራረሙን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡