የጉምሩክ ኮምሽን ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ድርጅት 30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረግ


ሰኔ 24/ 2013 (ዋልታ) –
የጉምሩክ ኮምሽን አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ከመላው ሀገሪቷ ከወደቁበት በማሰባሰብ እርዳታ በማድረግ ላይ ለሚገኘው የመቄዶኒያ የበጎ አድራጎት ድርጅት 30 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉ 26 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት አልባሳት እና የምግብ ነክ ቁሳቁስ እንዲሁም 3 ሚሊየን ብር በካሽ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ ድጋፉ መቄዶኒያ እያደረገ ላለው ድጋፍ በተለይም በዚህ ክረምት ወቅት ከፍትኛ አበርክቶ እንደሚኖረው በማመን መሆኑ ተናግረዋል፡፡
ኮምሽኑ በቀጣይም በሚቻለው አቅም መቄዶኒያ እያደረገ ያለውን የበጎ አድራጎት ተግባር ለመደገፍ ኮሚሽኑ ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ፕሬዘዳንት አቶ ቢኒያም በለጠ ለተደረጋለቸው ድጋፍ በአረጋውያን ስም አመስግነዋል እርዳታው በዚህ ክረምት መሆኑ የበርካታ አቅመደካሞችን ህይወት ሊያተርፍ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ቢኒያም ኮሚሽኑ ላደረገላቸው ድጋፉ የተሰማቸውን ደስታና አክብሮት ለመላ የኮሚሽኑ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች በመግለፅ በቀጣይም መቄዶኒያ በመላ ሀገሪቷ ለጀመራቸው ልማቶች ከጎኑ እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡