የጉራጌ ዞን ለመከላከያ ሰራዊት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ኅዳር 13/2014 (ዋልታ) የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍና ደጀን ለመሆን እስካሁን ከ101 ሚሊየን ብር በላይ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለፀ።
የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበርና ሌሎችም አገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በወልቂጤ ከተማ ውይይት እያካሄዱ ይገኛል::
በመድረኩ ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍና ደጀን ለመሆን ብሎም በግንባር ከመከላከያው ጋር በመሆን ለአገር ለመዋደቅ የዞኑ ህዝብና ወጣቶች፣ ከመከላከያ በክብር ተሰናባቾችና ተጠባባቂ ብሄራዊ ኃይሎች እንዲሁም አመራሩ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል።
ህዝቡን በተገቢው በማደራጀትና ግንዛቤ በመፍጠር የአካባቢን ሰላም መጠበቅና ማስጠበቅ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑም ተመላክቷል።
የተከፈተብን የኢኮኖሚ ጦርነት ለመመከትና እንደ አገር ሊያጋጥመን የሚችለው የምርት ጉድለት ለመሙላት የደረሱ ምርቶች አሰባሰብና ሌሎችም ወቅታዊ የመስኖ ስራዎችና የገቢ አሰባሰብ በትኩረት መምራት እንደሚገባ መገለጹን ከዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡