የጋና ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ በድጋሚ ምርጫ በማሸነፋቸው ተጨማሪ የአራት ዓመት የስልጣን ጊዜ እንዳገኙ የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የ 76 ዓመቱ አኩፎ አዶ 51 ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ጄን ሜንሳ ገልጸዋል።
ተቀናቃኛቸው ናሽናል ዴሞክራቲክ ኮንግረስ መሪ ጆን ማሃማ 47 ነጥብ 4 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውንም የኮሚሽኑ ሃላፊ አስታውቀዋል።
በ 38 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች 17 ሚሊየን መራጮች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን ፣ መራጮች ለብሔራዊ ፓርላማ 275 የሕግ አርቃቂዎች መምረጣቸውም ሲጂቲኤን አስነብቧል፡፡
አፍሪካ ህብረት፣ ኢኮዋስ እና የምዕራብ አፍሪካ የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት በጋራ በሰጡት መግለጫ የጋና ህዝብ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ በማከናወኑ አመስግነዋል።