የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሚያዝያ 29/2013 (ዋልታ) – የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ በሜካናይዜሽን ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለ4ኛ ዙር በኬኛ የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ የተገጣጠሙ 950 ትራክተሮችን ቁልፍ ለአርሶ አደሩ አስረክቧል።
በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በኬኛ የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ፋብሪካ ለ4ኛ ዙር የተገጣጠሙ 950 ትራክተሮችን በማህበር ለተደራጁ ወጣቶችና አርሶ አደሮች በስፋት ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም አርሶ አደሩ ከ30 እስከ 40 በመቶ በመቆጠብ የተቀረውን 60 በመቶ የግል ባንኮች ሊብሬ በመያዝ ማበደር በመቻላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን በ4 ዙሮች ብቻ ወደ 1ሺህ 687 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱንም የጠቆሙት ዶክተር ግርማ፣ በክልሉ 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት እየታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በትራክተር እየታረሰ ያለው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ወይም 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
950 የሚሆኑት ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ በመሰራጨታቸው ከ 20 በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ ማድረግ ያስችላልም ተብሏል።
ሆኖም አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም እንዲያርስ በመደረጉ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት መታረሱንና ይህንንም ቁጥር በቀጣይ ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማሳደግ በእቅድ መያዙን አመልክተዋል።
ትራክተሮችን ከውጭ በመግዛት ሀገር ውስጥ ከመገጣጠም ባለፈ በቀጣይ 5 አመታት ሙሉ በሙሉ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለማሳደግ እንደሚሰራ የክልሉ መንግስት ገልጿል።
የትራክተር መለዋወጫዎች ማለትም እንደ ማረሻ እና መከስከሻ ያሉትን ማሽኖች በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማምረት ፊልድ ኪንግ ከተሰኘ የህንድ ኩባንያ ጋር እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የትራክተር ጥገና ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑም ተነስቷል።
የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ በሜካናይዜሽን ግብርናውን በማዘመን አርሶ አደሩ በበሬ ከማረስ እንዲላቀቅ ይደረጋልም ተብሏል።
በዝግጅቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ፍፁም አሰፋ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌደራል መንግስት የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
(በደረሰ አማረ)