መጋቢት 02/2013 (ዋልታ) – የግብርና ሚኒስቴር ከሳኡዲ አረቢያው የቁም እንስሳት ንግድ ኩባንያ ጋር በኢትዮጵያ በ120 ሚሊየን ብር ወጪ በተገነቡ የቁም እንሰሳት ማዕከላት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለቀጣይ 10 ዓመታት ለመስጠት የመግባቢያ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴንና የሳዑዲ አረቢያው ሙሃመድ ሀሚድ ኤሊሳ የቁም እንስሳት ንግድ ኩባንያ ተወካይ ሱልጣን ጄይላን ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ኩባያው በሜሌ የቁም እንስሳ ማቆያ ማእከል የሚገኙ እንስሳት ለውጪ ገበያ ከመቅረባቸው በፊት የመቀለብ፣ የመመርመርና የመከተብ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ቀደም ሲል በሚሌ የቁም እንስሳ ማቆያ ማእከል በዓመት ከ60 ሺህ ያልበለጡ የቁም እንስሳት ለውጪ ገበያ ይቀርቡ እንደነበር እና አሁን የተገባው ስምምነትም እስከ 400 ሺህ የቁም እንስሳትን ወደ ውጪ ለመላክ እንደሚያሥችል በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡
በተጨማም የግብርና ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት 5 የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች ግዢ፣ ጥገና እና አስተዳደር የመግባቢያ ስምምነት ከናሽናል ኤርዌይስ ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴንና የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካፕቴን አበራ ለሚ ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ናሽናል ኤርዌይስ የ5 አውሮፕላኞች አቅርቦት፣ ጥገና እና የማስተዳደር አገልግሎቶችን የሚሰጥ ይሆናል፡፡
(በሳሙኤል ዳኛቸው)