የግብፅና ሱዳን ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነ ተገለፀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

 

ሚያዝያ 13/2013 (ዋልታ) – በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የግብፅና ሱዳን ኢ-ፍትሀዊ አካሄድ ተገቢ እንዳልሆነ እና ድርድሩ በአፍሪካ ህበረት ማእቀፍ ስር መቀጠል እንዳለበት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ የማስረዳት ስራ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ 62 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዘናል የሚለው የሱዳን መረጃ በሁለቱ ሀገራት መካከል ወታደራዊ ግጭት እንዳለ የማስመሰል ስራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በሳምንቱ በተከናወኑ የአገሪቱ ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ መግለጫውን የሰጡት አምባሳደር ዲና፣ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በቀዳሚነት ከተሰሩ ተግባራት መካከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የላኩትን ደብዳቤ ጨምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአውሮፓ ሚሲዮኖች ድርድሩ በአፍሪካ ማዕቀፍ ስር እንዲሆንና ስምምነቱ በግድቡ የውሃ ሙሌት ዙሪያ እንዲሆን ለአለም አቀፍ ተቋማት በቨርቿል ግንኙነት እንዳስረዱ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ-ሱዳን የድንር ውዝግብን አስመልክቶ ሱዳን 62 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዤ ለቅቂያለሁ የሚለው መረጃ በሀገራቱ መካከል ወታደራዊ ግጭት እንዳለ ለማስመሰል ያለመ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ዲና፣ ኢትዮጵያ አሁንም ለድንበር አለመግባባቱ ውይይትን አስቀድማ እንደምትሰራ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ በሰሜን አሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት በመካከለኛ ምዕራብ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ጋር መወያየታቸው አብራርተው፣ ዳያስፖራው 40 ሺህ ዶላር ለህዳሴ ግድቡ መዋጮ ማዋጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሳምንቱ በተሰራ የዜጎች ዲፕሎማሲ ስራዎችም 1 ሺህ 59 ስደተኛ ዜጎች ከተለያዩ የአረብ አገራት ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ተገልጿል፡፡
(በደምሰው በነበሩ)