የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የመሰረተ ልማት ግንባታ መከናወኑ ተገለጸ

ነሃሴ 05/2013 (ዋልታ) –የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች 600 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የጎርፍ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ ማከናወኑን ገልጿል።

የባለስልጣኑ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ ሥራዎች ላይ መክሯል።

ዐብይ ኮሚቴው ተቋማት በተናጠል ሲያከናውኑት የነበረውን ተግባር በማቀናጀት ስኬታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል ምክክር ማድረጉን ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ  በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት አጋጥሞ የነበረውን የጎርፍ አደጋ በመገምገም ምን ተሰራ በቀጣይስ ምን መስራት ይጠበቃል የሚሉት ጉዳዮች መዳሰሳቸውንም ገልጸዋል።

በ2012 ክረምት ያጋጠመውን የጎርፍ አደጋ መነሻ በማድረግ አሁን ሊደርስ የሚችልን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ሰፊ ስራ መሰራቱንም አመላክተዋል።

የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ፤ በ2013 ክረምት ኦሮሚያ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ጨምሮ በሌሎች ሰባት ክልሎች የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ 600 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጪ ለመሰረተ ልማት ግንባታ ውሏል ብለዋል።

አቢይ ኮሚቴው የጎርፍ ተጋላጭነትን የመቀነስ ስራውን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ ተቋማት የተካተቱበት እንደሆነም ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራው ኅብረተሰቡን ወደተሻለ ቦታ ማስፈርን ጨምሮ ውሃን በተፋሰስ መገደብና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውም ተገልጿል።

ተጋላጭነትን ለመቀነስም በፌዴራልና በክልል መንግስታት መካከል የግድብ አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማከናወን ቅንጅታዊ አስራር እየተፈጠረ መምጣቱም በጥንካሬ ታይቷል።

በመሰረተ ልማት ግንባታ ወቅት ያጋጠሙ የወሰን ማስከበርና የበጀት ውስንነት ችግሮች በቀጣይ ትኩረት እንደሚሹም ተመላክቷል።

በውይይቱ የዐብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የሌሎች ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።