የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ጉብንት በአምባሳደር ዲና መግለጫ

አምባሳደር ዲና

ነሐሴ 27/2013 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ጉብኝት ስኬታማ እንደነበረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ዲና በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሳምንቱ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶች መከናወናቸውን ገልጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሀገራቱ መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይሸል ኦማም ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮችን በራሷ መፍታት ትችላለች ማለታቸውን ተንግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኬንያ በአፍሪካ ህብረትም ይሁን በተባበሩት የጸጥታው ምክር ቤት መድረኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትሆን መናገራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራይሸል ኦማም ይህንን ያሉት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት እንደሆነም ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ በውይይታቸው የኢትዮጵያ ሰላም የኬንያ ሰላም መሆኑን እንዳነሱና ኬንያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እንዲሁም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የህግ ማስከበር ዘመቻን አስመልክቶ ኬንያ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን ገልጸዋል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ ኬንያ በጸጥታው ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበውላቸዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በኩል ከሳውዲ 2 ሺህ 900፣ ከቱኒዝያ 54 እንዲሁም ከየመን ኤደን 115 ዜጎች መመለሳቸውን አመልክተዋል።

(በመስከረም ቸርነት)