የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የመደመር ትውልድ” የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ

የመደመር ትውልድ

መጋቢት 9/2015 (ዋልታ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፃፈው “የመደመር ትውልድ” የተሰኘ መጽሐፍ በዛሬው ዕለት ተመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የፌዴራል እና ክልል ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምርቃት መርኃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሁነትን በጊዜው በመከተብ ታሪክን ለትውልድ ማስቀመጥን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመደመር ሀሳብ ላይ የሚያጠነጥን፣ የመደመር መንገድ በጉዞ የሚገለጥ እንዲሁም የመደመር ትውልድ የትውልድ ግንባታን የሚያመላክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፉ ትውልዱን “ወግ አጥባቂ፣ ህልመኛ፣ ውል አልባ፣ ባይተዋርና የመደመር ትውልድ” ሲል በአምስት ይከፍላቸዋል ብለዋል፡፡፡፡

ከእነዚህ መካከል የመደመር ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና በማሸጋገር ትልቅነቷን እንደሚያረጋግጥ እምነት የሚጣልበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ያለፈውን ማስተካከል፣ የዛሬውን ማስፋፋትና ፈተናዎችን ተሻግሮ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገን ማበርከት የመደመር ትውልድ ኃላፊነት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ትውልድ መቅረጽ ያስፈለገውም ፈተና ስላለ ነው ብለዋል፡፡

የመደመር ትውልድ በአቧራ የማይናወጥ ብቻ ሳይሆን አሻራ በማስቀመጥ ለቀጣዩ ትውልድ ከእዳ ይልቅ እድል መፍጠር የሚችል መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፈተናዎችን ተጋፍጦ በማለፍ የትናንት እና የነገውን ትውልድ ማገናኘት እንጂ ተስፋ ቆርጦ መቆም የመደመር ትውልድ ባህርይ አይደለም ነው ያሉት።

በመሆኑም የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሁነትን በጊዜው በመከተብ ታሪክን ለትውልድ ማስቀመጥን ያለመ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በቀጣይም የፖለቲካ ገበያውንና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ጦርነት በተመለከተ ሌላ መጽሐፍ ለማበርከት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የመደመር ትውልድ መጽሐፍ በሀሳብም በገንዘብም ትውልድ የሚሰራ በመሆኑ ገቢው ክልሎች ከመጽሐፉ ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ የመዝናኛ ስፍራዎችን ለመገንባትና ቅርሶችን ለማደስ እንዲጠቀሙበትም በስጦታ አበርክተዋል፡፡

መጽሐፉ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ሲሆን 274 ገፆች እንዳሉትና በሦስት ክፍሎችና በ10 ምዕራፎች የተዋቀረ መሆኑ ተገልጿል።

በደረሰ አማረ