የጠ/ሚ ዐቢይ የአልጄሪያ ጉብኝት ለሁለቱ አገራት የትብብር ግንኙነት ወሳኝ ነው – የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ

ነሐሴ 23/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአልጄሪያ ጉብኝት ለሁለቱ አገራት ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ ገለጹ።

በአልጄሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአልጀርስ የሰማዓታት መታሰቢያ ሙዚየም እና ግዙፉን ሳይዳል የመድሃኒት ፋብሪካ ጎብኝተዋል።

ከአልጀሪያ ፕሬዝዳንት አብዱልመጅድ ታቡኔ ጋር ሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአልጄሪያ ጉብኝት ለሁለቱ አገራት ጠንካራ የትብብር ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቀደም ሲል በአልጄሪያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም ለሁለቱ አገሮች የትብብር ግንኙነት መጠናከር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ተናግረዋ

ጉብኝቱ በአገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩንና ውጤታማ ትብብር ስለመኖሩም የሚያረጋግጥ መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

ሁለቱም አገራት የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ እልባት እንዲያገኙ በአፍሪካ ኀብረት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና አልጄሪያ የኢንዳስትሪ ልማት የተሻለ ዕድገት ለማምጣት ቁልፍ መሆኑን በመገንዘብ እየሰሩበት መሆኑንም ገልጸዋል።

አንድ ሉዓላዊ አገርና ሕዝብ የተፈጥሮ ሀብቱን የማልማት እና የመጠቀም መብት ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ መሰረትም የአፍሪካ አገራት መልካም ጉርብትና እንዲኖራቸውና ችግሮቻቸውንም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አልጄሪያ ትደግፋለች ብለዋል፡፡