የጡት ማጥባት ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ሊከበር ነው

ነሃሴ 3/2013(ዋልታ) – የጡት ማጥባት ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ16ኛ ግዜ ተከብሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ደግሞ በሚቀጥለው ረብዕ ይከበራል፡፡
የኦሮሚያ ጤና ጥበቃ ቢሮ ለሚዲያ በሰጠዉ መግለጫ ጡት ማጥባትን መጠበቅ የጋራ ሀላፊነት በሚል መሪ ቃል ከነሀሴ 5 እስከ ነሀሴ 12 2013ዓ.ም በኦሮሚያ ይካሄዳል ተብሏል።
የኦሮሚያ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ደረጅ አብደና የጡት ማጥባት ሳምንትን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደ ኢትዮጵያ ሆነ እንደ ክልሉ የህጻናት መቀንጨር አሳሳቢ መሆኑን አንስተው መቀንጨርን ለመከላከል በዋናነት ጡት ማጥባት ዋንኛ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
ሀላፊው አክለዉ የጡት ማጥባት ጥቅም ለሀገር እድገት እና የህብርተሰቡን ጤና ከማስጠበቅ አንፃር የጎላ ፋይዳ እንዳለው አንሰተዋል።
በኢትዮጵያ 37 በመቶ ህጻናት እንደሚቀነጭሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የቀነጨሩ ህጻናት በቀላሉ ለበሽታ ከመጋለጣቸው በተጨማሪ ትምህርት መቀበል አለመቻልን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን ያስከትልባቸዋል ያሉት ሀላፊው ይህን ተከትሎም ኢኮኖሚያዊ ችግር ያስከትላል ነው ያሉት፡፡
ልጆች በተወለዱ ባለው አንድ ሺህ ቀናት ወይም እስከ ሁለት ዓመት የተመጣጠነ ምግብ መመገባቸው ለዘላቂ ጤንነታቸው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ህጻናት ከተወለዱ እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት መጥባታቸው ደግሞ ለህጻናቱም ጤና ሆነ ለእናት ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
ለህጻናቱ በህጻንነት እድሜቸው ብቻ ሳይሆን ካደጉ በሆላ በሽታ እንዳይጋለጡ ያደርጋል በተለይ የአለም አሳሳቢ በሽታ የሆኑትን ተላላፊ ለሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትልቅ ጥቅም አለውም ነው የተባለው፡፡
በኢትዮጵያ እንዲሁም በኦሮሚያ ያለውን ጡት የማጥባት ልምድ ለማስጠበቅ በዘንድሮ ዓመት በሚከበረውም የጡት ማጥባት ሳምንት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀግብሮች ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡
(በእመቤት ንጉሴ)