የጣልቃ ገብ ኃይላትን ፍላጎት ለመቀልበስ የዲፕሎማሲ ሥራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋናው መስሪያ ቤት እና ከሚሲዮን ተመላሽ ዲፕሎማቶች፣ ለተጠሪ ተቋማት እና ከኤምግሬሽን ለተውጣጡ ሰራተኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ስልጠናው ዓለም ዐቀፋዊ እና አገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ከውጭ ግንኙነት ሥራዎች አንፃር ዙሪያ በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ኃላፊ ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት አደረጃጀት እና አሰራርና የጎረቤት አገራት ግንኙነት ዙሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተሰጥቷል።
ተገኝወርቅ (ዶ/ር) እንዳሉት አሁን ላይ በኃያላን አገራት መካከል የሚደረገው ሽኩቻ እየጨመረ መጥቷል።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት በድጋሚ ያገረሸው ፍጥጫ መቀጠሉ አይቀሬ እንደሆነ እና የተባበሩት መንግሥታትም ከመቼውም ጊዜ በላይ የኃያላን እና የጥቂት ጉልበተኞች መፈንጫ እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመተንተን በእውቀት የሚመራ ዲፕሎማሲ መከተል ይገባታል ያሉት ተገኝወርቅ (ዶ/ር) በቀጣናችን እና አጎራባች በሆነው የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና እየተካሔደ ያለውን ለውጥ በንቃት እየተከታተሉ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግም ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል።
ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭት እና የምጣኔ ሀብት አሻጥሮችን ለመዋጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የዲፕሎማሲ ሥራን በማጠናከር ጣልቃ ገብነትን የሚሹ ኃይላትን ፍላጎት መቀልበስ ይገባልም ብለዋል።
የአገሪቱ ዲፕሎማሲ ፈፃሚ ተቋማት እና ዲፕሎማቶች እነዚህን አደጋዎች በመመከት ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸውና በየጊዜውም አቅማቸውን እና ክህሎታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ኅብረት ምቹ መቀመጫ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው ይኸው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር እንደምትሰራ አንስተው ለዚህ ተፈፃሚነትም በአኅጉራዊና ቀጣናዊ ድርጅቶች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የምናደርገውን ጥረት የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አምባሳደር ተስፋዬ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
በስልጠናው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን እና ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተገኝተዋል።