የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የታየው ቸልተኝነት ዋጋ እያስከፈለ ነው አለ

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ

ታኅሣሥ 19/2014 (ዋልታ) የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የታየው ቸልተኝነት እና መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት እና የመደበኛ ክትባት አፈጻጸም ግምገማ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከመጡ የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ ከሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎች፣ ከአጋር አካላትና በኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት ዙሪያ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ጀምሯል።

በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት እና ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ግብአት በመመደብ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ እንደነበርና የመከላከያ ክትባቱንም አስር ሚሊየን ለሚጠጉ ሰዎች ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚመከሩ መከላከያ መንገዶችን ችላ በማለቱ እና ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ በመግባቱ በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

ይህም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ኅብረተሰቡ በኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ዙሪያ ግንዛቤውን እንዲያሳድግና ክትባቱን ጨምሮ ሌሎች የጥንቃቄ መንገዶችን እንዲያከብር ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ በጤና ተቋም በተገኘ መረጃ ብቻ 6 ሺሕ 800 የሚሆኑ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን እና በርካታ ዜጎችም ለጤና፣ ለማኅበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን አንስተዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን እና ሌሎች መከላከያ ምክሮችን ዜጎች ካለመዘናጋት እንዲጠቀሙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እስካሁን ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

ሌሎች የመደበኛ ክትባቶችም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም እንኳን ጥሩ አፈጻጸም እንዳለው አንስተው በተለይ የግጭት አካባቢ በነበሩ ስፍራዎች ትልቅ ስራ እንደሚጠይቅ እና በዚህ ዙሪያም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የግምገማ መድረኩ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደሚለይበት እና ለቀጣይ ስራ ግብአት የሚገኝበት እንደሆነ ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡