የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ዕውቅና ተሰጠ


ሐምሌ 16/2013 (ዋልታ) – የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጤና ባለሙያዎች እና ለእንክብካቤ ሰራተኞች የምስጋና እና የዕውቅና መርኃግብር አዘጋጅቷል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ማህበረሰቡ ከወረርሽኙ ለመዳን በቤት በቆየበት ወቅት የጤና ባለሙያዎች የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በጤና ተቋማት ውስጥ በስራ ላይ እንደነበሩ ይታወቃል።
ወረርሽኙ ያስከተለውን ጉዳት ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች እና የእንክብካቤ ሰራተኞች የበኩላቸውን በማድረግ እንደ ሀገር እስከ ህይወት መስዋዕትነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ተገልጿል።
በምስጋና መርኃግብሩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ እንዲሁም የከተማዋ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ለህይወታቸው ሳይሳሱ ወረርሽኙን ለመከላከል ላበረከቱት አስተዋፅኦ የጤና ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
በእውቅና እና የምስጋና ስነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ ጽህፈት ቤት፣ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶች እና በጎ ፈቃድ ቢሮ፣ የፋይናንስ እና ትምህርት ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች የተገኙ ሲሆን፣ ከጤና ጣቢያዎች ጀምሮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ለታካሚዎች የህክምና አገልግሎት በመስጠታቸው እውቅና እና ምስጋና ተችሯቸዋል።
በመርኃግብሩ ላይ በኮቪድ-19 ተይዘው ያገገሙ የጤና ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ለተደረገላቸው የህክምና እርዳታም ምስጋና አቅርበዋል።
(በቁምነገር አህመድ)